· ተነጋጋሪዎች ውይይቱን ለመቀጠል መስማማታቸውን አስታወቁ
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ በታንዛኒያ ሲካሔድ የነበረውን ውይይት አስመልክቶ፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ዛሬ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ “በታንዛኒያ ሲካሔድ የቆየው የሰላም ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ዛሬ ተጠናቋል፤” ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል ያለውን ግጭት በማስወገድ ሰላምን ለማምጣት የታለመበት እንደኾነ የተገለጸው ውይይቱ፣ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ መከናወኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገልጿል፡፡ ኾኖም፣ በመጀመሪያ ምዕራፍ ውይይቱ፣ ስምምነት ላይ ለመድረስ ያልተቻለባቸው አንዳንድ ጉዳዮች መኖራቸውን አልሸሸገም፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ “በአንዳንዶቹ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ ደርሰናል፤ በአንዳንዶቹ ደግሞ ገና መግባባት ላይ አልደረስንም፤ በአጠቃላይ ግን የውይይቱን ሌላ ምዕራፍ ለመቀጠል ተስማምተናል፤” ብሏል፡፡ ይኹን እንጂ ታጣቂ ቡድኑም ኾነ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን፣ ውይይት የተካሔደባቸውና በመግባባት በአለመግባባት የተጠናቀቁት ጉዳዮች ምን እንደኾኑ በርእስ ለይቶ አላብራራም፡፡
ያም ኾኖ፣ ግጭቱን በዘላቂነት እና ሰላማዊ በኾነ መንገድ ለማስቆም እንዲቻል፣ ሁለቱም አካላት የሰላም ውይይቱን የመቀጠል አስፈላጊነት ላይ መግባባታቸውን፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡ ውይይቱ መቼ እና የት እንደሚቀጥል ግን አልተጠቀሰም፡፡
መግለጫው፣ “በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና እስከ አሁን ሲመራባቸው በነበሩ መሠረታዊ መርሖች መሠረት፣ ግጭቱን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት፣ መንግሥት የጸና አቋም አለው፤” ሲልም የመንግሥትን አቋም አስታውቋል።
የሰላም ውይይቱን ለአመቻቹና ለአስተናገዱ አካላትም፣ መንግሥት ምስጋናውን ያቀረበ ቢኾንም፣ የውይይቱ አመቻቾች እና አወያዮች፣ እንዲሁም ከሁለቱም ወገኖች በውይይቱ ላይ የተሳተፉት እነማን እንደኾኑ በዝርዝር አልጠቀሰም፡፡
ምንም እንኳን መንግሥት ተወያዮቹን ባይጠቅስም፣ ከመንግሥት ወገን በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት አካላት መካከል እንደኾኑ የሚነገርላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ በመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከወጣው መግለጫ ጋራ ተመሳሳይነት ያለው ጽሑፍ፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡ ይኹን እንጂ፣ ስለ ውይይቱ ዝርዝር ነገር አላነሡም፡፡
ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፣ ስለ ውይይቱ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረትም፣ የመሥሪያ ቤቱ ባለሥልጣናት ስልክ ባለመነሣቱ ሊሳካልን አልቻለም፡፡
በተያያዘ፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) እና የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን፣ ትላንት ባወጡት መግለጫ፣ መንግሥት ግልጽ የኾነ የውይይት እና የፖለቲካ አካሔድን አለመከተሉን ነቅፈው፣ ይህም የተለያዩ የጸጥታ ችግሮችን እያስከተለ እንደኾነ አመልክተዋል፡፡
ኢዜማ በመግለጫው፣ መንግሥት ስለ ታንዛኒያው ውይይት ግልጽ የኾነ መረጃ እንዲሰጥ ሲጠይቅ፤ አብን በበኩሉ፣ በዐማራ ክልል ያለው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ ለብዙ ዓመታት የትጥቅ ትግል ሲያካሒድ የቆየው ኦነግ አመራሮች፣ በተለያየ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምረዋል። በዚኽ ወቅት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ ከግንባሩ ተገንጥሎ የወጣ ቡድን መኾኑን አስታውቆ ነበር። ይህ ታጣቂ ቡድን፣ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከመንግሥት ወታደሮች ጋራ ውጊያ እያካሔደ እንደሚገኝ፣ የቡድኑ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ በተለያየ ወቅት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸው ነበር።
ለሁለት ዓመታት የዘለቀውና በብዙ መቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከስድስት ወራት በኋላ፣ ሚያዝያ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል ስያሜ ከህወሓት ጋራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ተፈረጀ።ከሰላም ስምምነቱ መፈረም በኋላ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ የኢትዮጵያ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባካሔደው ልዩ ስብሰባ፤ ህወሓት ከሽብር ዝርዝር ውስጥ እንዲሰረዝ በአብላጫ ድምፅ ወስኗል። የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ግን፣ አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ በአሸባሪነት የተፈረጀ ድርጅት ነው።
በሌላ በኩል፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ጥቃቶች፤ ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ደግሞ የዐማራ ተወላጆችን ለይቶ ያጠቃል፤ ከመኖሪያ ቀዬአቸውም ያፈናቅላል፤ በሚል ክሥ ይቀርብበታል። ቡድኑ በተደጋጋሚ፣ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እንዳልፈጸመ ቢያስተባብልም፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው ተፈናቃዮች ግን፣ የጅምላ ግድያ እና ማፈናቀል፣ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በሚጠራ ታጣቂ ቡድን እንደተፈጸመባቸው ሲገልጹ ቆይተዋል።
አምነስቲ ኢንተርናሻል ባለፈው ወር በአወጣው ሪፖርት፣ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ፣ በአንድ ቀን ከ400 በላይ ሰላማውያን የዐማራ ተወላጆች ተጨፍጭፈው መገደላቸውንና ለግድያውም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ተጠያቂ ማድረጋቸውን፣ ከጥቃቱ የተረፉ እማኞቹን ጠቅሶ ነበር። በዐማራ ብሔር ተወላጆች ላይ፣ በኦሮምያ ክልል የተፈጸመውና “አሠቃቂ” ብሎ የገለጸው ግድያ እንዲመረመርም የመብት ተሟጋች ድርጅቱ ጠይቆ ነበር።