በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ ተገለጸ


በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳግም መቀስቀሱ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:26 0:00

በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልልን የሚያስተዳድሩ ባለሥልጣናት፤ “የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ መጠን ያለው ጥቃት አደረሰብን” ሲሉ ዛሬ መግለጫ አውጥተዋል።

ይህን ክስ ያጣጣለው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ ጥቃት የከፈተው ህወሓት መሆኑን ገልጿል፡፡ ጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱ ይፋ በሆነበት በዛሬው ዕለት፣ የጦር መሳሪያ ጭኖ በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ ሲገባ የነበረ አውሮፕላን ተመትቶ መጣሉንም የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል፡፡

የጦር መሳሪያ ጭኖ በሱዳን በኩል የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ ሲገባ የነበረ አውሮፕላን በኢትዮጵያ አየር ኃይል ተመትቶ መውደቁን የመንግሥት ምንጮች አስታውቀዋል፡፡

አውሮፕላኑ ለህወሓት ኃይሎች የጦር መሳሪያ ጭኖ ሲጓዝ እንደነበረ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደሕንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት አጭር ጹሑፍ ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ አምባሳደር ሬድዋን በዚህ ጹሑፋቸው “የሃገራችን ታሪካዊ ጠላቶች ንብረት የሆነ አውሮፕላን መሳሪያ ጭኖ መቀሌ ሲያራግፍ ተመቶ መጣሉን መከላከያ ገልጿል” ብለዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የመከላከያ ህብረት ዘመቻ ዋና መምሪያ የመከላከያ ኃይል ስምሪት ኃላፊ ሜጀር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌውን ጠቅሶ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ባወጣው ዘገባ ደግሞ “በሱዳን አድርጎ የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ በሁመራ ሰሜናዊ ክፍል በኩል ወደ ትግራይ ሊያልፍ የነበረና ለህወሓት የጦር መሳሪያ ሊያቀበል የነበረ አውሮፕላን በአየር ኃይል ማታ አራት ሰዓት ላይ ተመትቶ መውደቁን” አመልክቷል፡፡

የትግራይ ክልል የውጭ ግንኙነቶች ቢሮ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያን አየር ክልል ጥሶ በመግባት በትግራይ ክልል መሳሪያ ሲራግፍ የነበረ አውሮፕላን የኢትዮጵያ መንግሥት መትቶ ጥሏል ማለታቸውን አጣጥሏል። "ወደ ትግራይ የገባ አውሮፕላን የለም፣ ተመትቶ የወደቀ አውሮፕላንም የለም" ያለው መግለጫ "የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ላይ የአየር ጥቃት ለማድረግ ሁኔታዎችን እያመቻቸ ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

አውሮፕላኑ ግዛቷን አቋርጦ እንዳለፈ ከተጠቀሰችውና ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ምክንያቶች አለመግባባት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን በኩል ግን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነቱ ዳግም መቀስቀሱ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳስደነገጣቸው እና እንዳሳዘናቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ አስታውቀዋል።

የትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ እና አፋር ክልል ነዋሪዎች እስካሁን ከፍተኛ ስቃይ እንደደረሰባቸው ያስታወሱት ዋና ጸሐፊው "ጥቃቱ ባስቸኳይ እንዲቆም እና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በህወሓት መካከል የሰላም ውይይት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት እንዲቀጥል አሳስበዋል።

ሰብዓዊ እርዳታ ለሁሉም እንዲዳረስ እና መሰረታዊ አገልግሎቶች እንዲቀጥሉ ተማፅኖ አቅርበዋል።

ከአንድ ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ተፈፀመ የተባለው ጥቃት የሰላም ውይይት ለማካሄድ እና ምግብ እና መሰረታዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት የሚያሰናክል ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።

በኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ኃይሎች እና ትግራይን በሚያስተዳድረው ህወሓት ኃይሎች መካከል ቆቦ ከተማ አካባቢ ዛሬ ሌሊት ውጊያ መጀመሩን ነዋሪዎች ለሮይተርስ ገልፀዋል። ለጦርነቱ መቀስቀስ ሁለቱም ወገኖች እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ ነው።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ባወጣው መግለጫ ዛሬ ጠዋት ከለሊቱ 11 ሰዓት አካባቢ ህወሓት በምስራቅ ግንባር በሚገኙ ብሶበር፣ ዞብል እና ትኩልሽ አቅጣጫ ጥቃት ማድረሱን አስታውቋል።

የትግራይ ወታደራዊ ኮማንድ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት የተኩስ ማቆም ሥምምነቱን መጣሱን አስታውቆ በደቡብ አቅጣጫ የተደረገው ጥቃት ማሳሳቻ እንደነበር እና ሰራዊታቸው ከምዕራብ አቅጣጫ ከፍተኛ ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል አውቆ እንደነበር አመልክቷል።

ሮይተርስ ያናገራቸው ሦስት ነዋሪዎች ከጠዋት ጀምሮ የከፍተኛ መሳሪያ ድምፅ መስማታቸውን እና የአማራ ልዩ ኃይል እና የፋኖ ሚሊሺያን ያካተተ የኢትዮጵያ ሰራዊት ላለፉት ሁለት ቀናት ሲንቀሳቀሱ ማስተዋላቸውን ገልፀው ጦርነቱን ማን እንደጀመረ ግን እንደማያውቁ አስረድተዋል።

ከአንድ ዓመት በላይ በትግራይ ክልል የስልክ ግንኙነት ባለመኖሩ ሮይተርስ በትግራይ ኃይሎች በኩል ያለውን እንቅስቃሴ ማጣራት አልቻለም።

XS
SM
MD
LG