- በብሔራዊ ደኅንነት ሓላፊው መመራቱ ትኩረት ስቧል
የሀገረ ኤርትራ ከፍተኛ ወታደራዊ ባለሥልጣናትን የያዘ ልኡክ፣ የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ የጸጥታ ተቋማትንና የሕዳሴ ግድብን ጎብኝቷል።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ፣ የኹለቱን አገሮች ወታደራዊ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ያለመ እንደኾነ፣ የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር ገልጸዋል።
በኤርትራው የብሔራዊ ደኅንነት ተቋም ሓላፊ በብርጋዴር ጀነራል ኣብርሃ ካሳ የተመራ የጀነራል መኰንኖች ቡድን፣ ባለፉት ኹለት ቀናት፣ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጉን፣ የኤርትራ መንግሥት ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረ መስቀል በትዊተር ገጻቸው አስታውቀዋል።
የጉብኝቱ ዋና ዓላማ፣ የኹለቱን አገሮች ወታደራዊ ትብብር በይበልጥ ለማጠናከር እንደኾነ የገለጹት አቶ የማነ፣ ቡድኑ ከትላንት በስቲያ፣ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ዋና ከተማ አሶሳንና ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጎብኘቱን ጠቅሰዋል። ቡድኑ፣ በትላንትናው ዕለት ደግሞ፣ የኢትዮጵያን የመረጃ መረብ እና ደኅንነት ኤጀንሲ፣ የአርተፍሻል ኢንተለጀንስ ተቋም፣ የፌደራል ፖሊስ ዋና መሥሪያ ቤት፣ የሳይንስ ሙዚየም እና አብርሆት ቤተ መጻሕፍትን መጎብኘቱን ሚኒስትሩ አትተዋል።
ይኸው የጀነራል መኰንኖች የሥራ ጉብኝት፣ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈ ወርቂ የቅርብ ሰው በኾኑት ብርጋዲየር ጀነራል ኣብርሃ ካሳ መመራቱ፣ ከፍ ያለ ቁም ነገር ለመያዙ አመልካች እንደኾነ፣ የኤርትራ መንግሥት ምንጮች አስገንዝበዋል።
በከፍተኛ ወታደራዊ ልኡኩ ከተካተቱት መሀከል፥ ሜጀር ጀነራል ሮመዳን አውዲያ፣ ብርጋዲየር ጀነራል ሓዱሽ ኤፍሬም፣ ብርጋዲየር ጀነራል ኢዮብ ፍሥሓየ እና ብርጋዲየር ጀነራል ሚካኤል ሓጎስ እንደሚገኙበት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፣ በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አስተያየት ለማግኘት ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም።
ከዚኹ ጉብኝት ኹለት ሳምንታት አስቀድሞ፣ የኤርትራ መከላከያ ኀይል እና የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በቅርቡ የሰሜን ጦርነት፣ የጦር ወንጀል መፈጸማቸውንና በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ፣ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው። ክሡን እንደማይቀበል የገለጸው የኤርትራ መንግሥት በበኩሉ፣ "የኤርትራ እና የኢትዮጵያ ሕዝቦች እንዲሁም የአካባቢው ሕዝቦች፣ ለችግሮቻቸው መፍትሔ ለመፈለግ፣ መብቱም ብቃቱም አላቸው፤ በማለት ክሡን አጣጥሎታል።