በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የአንድ ሰው አገዛዝ እንዳይሆን የሠጉ አሉ


ኢሕአዴግ ስምንተኛ መደበኛ ጉባዔውን አጠናቀቀ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስና ወጣት መንግሥት ይመሠርታሉ እየተባለ ነው፡፡

የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ በሣምንቱ ውስጥ ስምንተኛ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ ጉባዔው ፓርቲውን በወጣት አመራር ለመተካት በሚቻልበትና ተስፋ በጣለበት የአምስት ዓመት የምጣኔ ኃብት ዕቅድ ላይ ለመነጋገር ነው አጀንዳ የያዘው፡፡ አዲሱ የፓርቲው አደረጃጀት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሥልጣን የሚያጠናክር እንደሚሆን ተንታኞች ይናገራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ስምንተኛ መደበኛ ጉባዔን ያስጀመሩት ሃገሪቱ የኖረችበትን የውጭ ምግብ ዕርዳታ ጥገኝነት በመጭዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ለመስበር ቃል በመግባት ነበር፡፡

በርግጥ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተስፋ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ካሣለፈችው ሕይወቷ ጋር ፊት ለፊት የሚጣረስ ነው፡፡ የተራዘመው ረሃብ አሁንም ቢሆን ከስድስት ኢትዮጵያዊያን አንዱን ረሃብተኛ ያደረገበት ጊዜ ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ብቻዋን እንኳ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከግማሽ ቢልዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና ሸቀጣ ሸቀጥ አቅርቦቶች ያስገባችበት ዓመት ነው ያለፈው፡፡ ይህ በቀድሞው ምንዛሪ እንኳ ሲሰላ ወደ ሰባት ቢልዮን የኢትዮጵያ ብር የሚጠጋ ገንዘብ መሆኑ ነው፡፡

ይህ የአዳማ ጉባዔ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የሽግግር ዕቅድ በይፋ የሚገለጥበት፣ የአቶ መለስ ዜናዊ የኢሕአዴግ መሪነት፣ "የአንድ ፓርቲ የበላይነት" እያሉ በሚጠሯት ሃገር ላይም መንበረ ሥልጣኑን እንደጨበጡ እንደሚቀጥሉ በድጋሚ የሚረጋገጥበት ይሆናል ተብሎ ነው የሚጠበቅ፡፡

ይህ ስብሰባ የተጠራው ፓርቲው ዋና የሚባል ለውጥ በራሱ ላይ እያካሄደ መሆኑ በሚነገርበት ወቅትም ነው፡፡ አቶ ስዩም መስፍንን የመሣሰሉትን ጨምሮ አንጋፋ ናቸው የሚባሉ የግንባሩ ሰዎች ብርቱ ናቸው ከሚባሉቱ የአካባቢ የፖለቲካ ቢሮዎች ሁሉ መውጣታቸው ተሰምቷል፡፡ አቶ መለስ በሚቀጥለው ወር ያደርጉታል በተባለ ሹም ሽር አዳዲስ ፊቶችን በመንግሥታቸው ውስጥ ለማስተናገድ መዘጋጀታቸውንም ሲጠቋቁሙ ተደምጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ ያ ብወዛ ምን እንደሚያመጣ፣ እነማን እንደሚወጡ፣ እነማን እንደሚወድቁ ብዙም የሚታወቅ ነገር የለም - አሁን ላለው ጊዜ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን አቶ መለስ የቀድሞ የትግራይ ሽምቅ ንቅናቄ ጓዶቻቸውን ዘወር አድርገው በአዳዲስና ወጣት የፓርቲ ታማኞች ቢተኳቸው የሚከተለው ነገር ቢኖር እንዲሁም የሙጥኝ ብለው የጨበጡትን ሥልጣን የሚያጠናክርላቸው እንደሚሆን የአፍሪካ ቀንዱ የፖለቲካ ተንታኝ መድኀኔ ታደሰ ሲናገሩ

"አዲሶቹ የምንላቸው ሰዎች መምጣት ከለውጥ ወይም ሂደቱን ከመቀየር ይልቅ ባለበት ሁኔታ የሚያጠናክረው ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም መለስ ሃሣቦቻቸውን የሚያቀርቡት ለድሮ ጓዶቻቸው ሳይሆን ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ለተሰባሰቡ፣ አንዳችም የትግልም ይሁን በራሣቸው የያዙት የፖለቲካ ማንነት ለሌላቸው አዳዲሶቹ ሰዎች ነው፡፡ በመሆኑም ይህ እርምጃ የግል ተፅዕኗቸውን የሚያጠናክርላቸው ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደጎሉ የሚቀጥሉት የርሣቸው የግል ሃሣቦች፣ የርሣቸው ተክለማንነት ይሆናሉ፡፡" ብለዋል፡፡

ይህ ሥልጣንን የመሰባሰብና የማጠናከር አዝማሚያ ሃገሪቱን ወደ አንድ ግለሰብ አገዛዝ ሥርዓት እንዳይወስዳት ይሠጋሉ መድኀኔ፡፡ እንዲህ አሉ፡-

"በቅርብ ጊዜው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሣዛኝ የሆነው ጉዳይ መንግሥቱም፣ ገዥ ፓርቲውም፣ ሕግ አውጭውም ሁሉም አንድና እርሱው መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ውስጥ አንድ ብርቱ የሚባል ሰው መኖር የሚያሣየው እንዲያው እንደወትሮው ዓይነት የሃገርን፣ የገዥ ፓርቲንና የመንግሥትን መጣጣም አይደለም፡፡ ባለፉት ዓመታት ጉዞ ውስጥ የጋራ አመራር የሚባል ነገር ተመናምኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርቲያቸው ውስጥ ብቻ ሣይሆን ዛሬ በደረስንበት ሁኔታ በሃገሪቱና በመንግሥቱ መዋቅሮች ውስጥ በሚከናወነው ሥራ ሁሉ ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭ ሆነዋል፡፡"

ኢሕአዴግ በለውጥ እንደገና ለመደራጀት የያዘው አቋም "ደፋር እርምጃ" ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሣይንቲስት ሰሎሞን መብሬም ቢሆኑ ሥጋት አላቸው፡፡ በፓርቲና በመንግሥት መካከል ግልፅ የልዩነት መሥመር ያለመኖሩ ጉዳይ ለሙስና መቀፍቀፍ ምቹ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

"በመንግሥትና እንደ ፖለቲካ ድርጅት ደግሞ በኢሕአዴግ መካከል መኖር ይገባው የነበረው ልዩነት በውል እንዳይታወቅ የመደብዘዙ ጉዳይ የተወሰኑ የመንግሥት አሠራሮች እና በታች ደረጃ ያሉ አባላቱ ለግል መግነኛ በመሣሪያነት እንዲጠቀሙበት አስችሏል፡፡ ይህም የተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት መርሆች በከባዱ ተጨፈላልቀው ለአስተዳደሩ መበላሸት ዋና በሚባል ሁኔታ አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡" ብለዋል ሰሎሞን መብሬ፡፡

መለስ ከቻይና ኮምዩኒስት ፓርቲ የተጋበዙ ተወካዮችን፣ የሕንድ መንግሥት አባላትን፣ እንዲሁም አጋር የተባሉ የየመን፣ የሱዳን እና የሞዛምቢክ ድርጅቶች እንግዶችን በደስታ እየተቀበሉ ማስተናገዳቸውን የመንግሥቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ይህ የውጭ እንግዶች ዝርዝር የኢትዮጵያን ቅድሚያዎች ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ እየተሸጋገረ መምጣት ያንፀባርቃል ይላሉ ተንታኙ መድኀኔ ታደሰ፡፡

"ምንም እንኳ ምዕራቡ የገንዘብ አቅም ቢኖረውም በሃገር ውስጥ ባለው ፖለቲካ ላይ ግን ጫና የማሣደር ጉልበት እንደሌለው የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ የተረዳ ይመስለኛል፤ - አሉ አቶ መድኀኔ - ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን የምዕራቡን ድጋፍና የልማት እርዳታ ትፈልጋለች፤ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉትን እንደ ቻይናና ሕንድ አይነቶቹን ኃያላን ቦታም ደግሞ ትገነዘባለች፡፡ ጉዳዩ መርህና ርዕዮተ ዓለም ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የመመቻቸት ወይም የመጠቃቀምም ጉዳይም ነው፡፡" ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ እጅግ ከሰሉ የመለስ ተቺዎችና ነቃፊዎች መካከልም "ከአፍሪካ ጠንካራ መሪዎች አንዱ ናቸው" ብለው የሚናገሩላቸውም አሉ፡፡ 'የኢትዮጵያን ገፅታና ዝና በዓለም አቀፍ ደረጃ አንስተዋል፣' ይሉላቸዋል፡፡ ቡድን ሃያ እየተባለ በሚታወቀው የሃያዎቹ እጅግ ከበርቴ ሃገሮች ስብሰባዎች ላይ አፍሪካን እየወከሉ መገኘታቸውን፣ ዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሃገን ላይ ተደርጎ በነበረውና የፊታችን ታኅሣስ ውስጥም ካንኩን - ሜክሲኮ ላይ በሚቀጥለው የዓለም የአየር ንብረት ጉባዔዎች ላይ የአፍሪካን ቡድኖች መምራታቸውን ያነሣሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሚቀጥለው ሣምንት ኒው ዮርክ ላይ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመገኘት ወደዚያው ያመራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በዚያውም በኒው ዮርኩ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው የዓለም መሪዎች መድረክ ላይ ንግግር ሊያደርጉ በመርኃ-ግብሩ ላይ ሠፍረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመድረኩ ላይ እንዲናገሩ መጋበዛቸው በተለይ በብዙ በውጭ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ብርቱ ተቃውሞን መቀስቀሱ እየተነገረ ነው፡፡(የዘገባው መጨረሻ)

XS
SM
MD
LG