በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

መንግሥት ከቁጣ ቀስቃሽ ርምጃዎች ውይይትን እንዲያስቀድም የአረፋ በዓል ታዳሚ ምእመናን ተናገሩ


መንግሥት ከቁጣ ቀስቃሽ ርምጃዎች ውይይትን እንዲያስቀድም የአረፋ በዓል ታዳሚ ምእመናን ተናገሩ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:04 0:00

መንግሥት፣ የሕዝብን ቁጣ በሚቀሰቅሱ ጉዳዮች ላይ ርምጃ ከመውሰዱ በፊት፣ ውይይትን ሊያስቀድም ይገባል፤ ሲሉ፣ በዐዲስ አበባ ከተማ በተከበረው የአረፋ በዓል የሶላት ሥነ ሥርዐት ላይ የተገኙ አስተያየት ሰጪዎች ተናገሩ፡፡ 1ሺሕ444ኛው የዒድ አል አድሃ(አረፋ) በዓል፣ ዐዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ኢትዮጵያ ተከብሮ ውሏል፡፡

በዓሉ፣ ከመሳጂዶች ፈረሳ ጋራ በተያያዘ የተፈጠሩ አለመግባባቶች፣ በውይይት እንደተፈቱ ከተገለጸ ከሳምንታት በኋላ ነው የተከበረው፡፡ በዐዲስ አበባ ከተማ፣ በርካታ የእምነቱ አባቶች እና ተከታዮች፣ በስታዲየም እና አካባቢው ተገኝተው፣ የሶላት ሥነ ሥርዐት አካሒደዋል፡፡

የአረፋ በዓል፣ ነብዩ ኢብራሂም፣ ልጃቸውን ለፈጣሪ ለመሠዋት በመታዘዝ፣ ከኹሉም በላይ የኾነውን የፈጣሪ ፍቅር ያሳዩበት ታላቅ በዓል መኾኑን የሚገልጹ አስተያየት ሰጪዎች፣ በዓሉን ከችግረኞች ጋራ በፍቅር እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል፡፡

የዘንድሮው የአረፋ በዓል የሚከበረው፣ በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በመንግሥት ከተፈጸመው የመሳጂዶች ፈረሳ ጋራ በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት፣ በኦሮሚያ ክልል መንግሥት እና በመጅሊስ መካከል ውይይት ተደርጎ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው፡፡

በርካታ ሙስሊሞች፣ የመሳጂዶቹን ፈረሳ በመቃወም ቁጣቸውን እንደገለጹ እና በተለይ በዐዲስ አበባ ከተማ፣ ፖሊስ በወሰደው ርምጃ፣ የሰዎች ሕይወት እንዳለፈ ይታወቃል፡፡

መንግሥት፣ ከሕዝብ ጋራ ውይይት ሳያደርግ በተናጠል ርምጃ መውሰዱ፣ የችግሩ ዋና መንሥኤ እንደኾነ ያስረዱ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከሰሞኑ ክሥተት መማር እንደሚያስፈልግ ያሳስባሉ፡፡

የዛሬው የአረፋ በዓል የሶላት ሥነ ሥርዐት፣ በሰላም እንደተጠናቀቀ፣ የጸጥታ እና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል፡፡

ሙሉ ዘገባውን ከተያያዘው ፋይል ያዳምጡ።

XS
SM
MD
LG