በኢትዮጵያ የሐምሌ ወር የዋጋ ግሽበት ወደ 22.3 በመቶ ማሻቀቡን የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ አሳውቋል። ላለፉት ሶስት ተከታታይ ወራትም በሀገሪቱ የዋጋ ግሽበት እየጨመረ መሄዱን የማዕከሉ መረጃ አመልክቷል። ለዋጋ ግሽበቱ መጨመር ቀዳሚ ምክንያት የሆነው በምግብ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ሲሆን ይህም ወደ 23.7 በመቶ ከፍ ማለቱ ታውቋል። እየበረታ የሄደው የዋጋ ጭማሪ በህበረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ መሆኑንም ነዋሪዎችና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያስረዳሉ። የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ በምግብ ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ በምርት ማነስ የተፈጠረ ሳይሆን የገበያው ሰንሰለት ስርዓት አለመኖር ያመጣው ህገ-ወጥነት ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ንረት በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩትን የሀሪቱን ዜጎች ብርቱ ፈተና ውስጥ ከቷቸዋል። በተለይ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ የእህል፣ የጥራጥሬና የአትክልት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሄድ በህብረተሰቡ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው።
ይህ የዋጋ ንረት ቀጥተኛ ተፅእኖ ካደረሰባቸው ነዋሪዎች መሃል ወይዘሮ ምጥን ፍሰሀ እና ቤተሰቦቻቸው ይገኙበታል። በአዲስ አበባ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ምጥን ትራንስፖርት ባለስልጣን ተቀጥረው በሚያገኙት ገንዘብ እራሳቸውን ጨምሮ ከስድስት በላይ የሆኑ የቤተሰባቸውን አባላት ለማስተዳደር መቸገራቸውን ይገልፃሉ።
በኢትዮጵያ እየታየ ላለው የዋጋ ግሽበት ዋና ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው የምግብ ነክ ሸቀጦች፣ በተለይ የእህል ዋጋ መናር ነው። በማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ መሰረት የምግብ ዋጋ ግሽበት 23.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን ካለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በ 24.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በጉዳዩ ላይ ያናገርናቸው የኢኮኖሚ ባለሙያ አቶ ብስራት ተሾመ፣ ለዋጋ ጭማሪ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች አንዱ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ መሰረት አልባ ግምታዊ ምልከታዎች (Speculation) መሆናቸውን ያስረዳሉ።
በሀገሪቱ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የእህል ምርት አቅርቦት ችግር እንደሌለ የሚያስረዳው የግብርና ሚኒስቴር ባለንበት የምርት ዘመን ከታቀደው 1.9 ሚሊዮን ሄክታር በላይ 2.1 ሄክታር ዘር ተዘርቶ ምርት መሰብሰቡን ይገልፃል። በሚኒስቴር መስሪያቤቱ የሰብል ልማት ዳይሬክተር የሆኑት ኢሳያስ መና ለአሜሪካ ድምፅ ሲያስረዱ የአቅርቦት ችግሩ የሚፈጠረው 'ስግብግብ' ብለው የሚጠሯቸው ነጋዴዎች ጋር ነው ይላሉ።
አሁን ባለው ነጋራዊ ሁኔታ ግን ወይዘሮ ምጥንና እና ቤተሰቦቻቸውን ቀድሞ ይመገቧቸው የነበሩ የምግብ አይነቶችን እንዲቀንሱ ወይም ከነጭራሹ መመገብ እንዲያቆሙ እያስገደዳቸው ነው። ከምግብ ዋጋ በተጨማሪም የትራንስፖርት፣ የመብራት፣ የውሃ እና የመሳሰሉት ዋጋዎች ንረት እጅግ እንዳማረራቸው ወይዘሮ ምጥን ያስረዳሉ።
አገር ውስጥ ከሚታየው የእህልና ሌሎች የምግብ ውጤቶች ዋጋ መናር በተጨማሪ መንግስት በተደጋጋሚ የብር ምንዛሬ ተመን እንዲቀንስ ማድረጉ ከውጪ lሚመጡ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ መጨመርና ለዋጋ ግሽበትቱ ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። አቶ ብስራት ይህ በተለይ በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ ተጨማሪ ተፅእኖ ያደርሳል ይላሉ።
ልክ እንደውይዘሮ ምጥን የኑሮ ውድነት ከአቅማቸው በላይ የሆነባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በብዛት እንደሚታዩ የሚያስረዱት አቶ ብስራት በዚህ ከቀጠለ ህብረተሰቡን ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዳይገፋውም ስጋታቸውን ያጋራሉ።
በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚታየው የፖለቲካ አለመረጋጋትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝም በሸቀጥ አቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ ንዝረት ከሚያስከትሉ ጉዳዮች አንዱ መሆናቸውንም የኢኮኖሚ ባለሙያው ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገሪቱ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ወደ አንድ ነጠላ አኃዝ አውርዶ የዋጋ መረጋጋት ለማምጣት እንደሚጥር ባሳለፍነው የበጀት ማጠናቀቂያ ላይ ቢገልፅም ላለፉት ሁለት አመታት የዋጋ ግሽበቱ ከሁለት አኃዝ መውረድ አልቻለም። ይህን ለማረጋጋት መንግስት ምግብ ነክም ሆኑ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ወደ ገበያ በብዛት እንዲገቡ የማድረግና በአቅርቦት ሰንሰለቱ ላይ የተሰማሩ አካላት ውስኔ ሰጭነት ከመሀል አውጥቶ አምራቹና ተጠቃሚው የሚገናኙባቸው መንገዶች ላይ አተኩሮ እንዲሰራ አቶ ብስራት ይመክራሉ።
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።