በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኢትዮጵያ ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ የሚዳሩ ሴት ልጆች


በኢትዮጵያ እድሚያቸው ሳይደርስ የሚያገቡ በሽሕ የሚቆጠሩ ሴት ልጆች በርካታ ናቸው። ከጎንደር የአሜሪካ ድምጿ ማርተ-ፋንደር ቮልፍ እንደዘገበችው ዩኒሴፍና የአካባቢው ባለስልጣናት በአካባቢው ማህበረሰብ ግንዛቤ ለማስጨበጥ መጠነ ሰፊ ስራ ጀምረዋል።

የዐሥራ ስድስት ዓመቷ ታዳጊ ህብስት አበባየሁ ከሦስት ዓመታት በፊት ጎንደር ከተማ በሚኖር የሃያ ስምንት ዓመት ወጣት ታጭታ ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ፤ ቤተሰቦቿ ሌላ ጠያቂ ተገኘ ብለው ሊድሯት ደፋ ቀና ሲሉ ነበር የከረሙት።

ሽምግልናው በህብስት ላይ ሲደራ፤ ማንም ሰው ታዳጊዋን በራሷ ኑሮ ያገባታል ብሎ ያማከራት የለም። እንዲያውም መታጨቷንም፤ ጠያቂ መምጣቱንም የምትሰማው ጓደኞቿ ሲያወሩ ነው።

“ከዚያ ሊድሩኝ፣ ደሞ እኛ ዘንድያ ማለት ነው ከድሮውንም መኼድ ተማሪዎች በጣም ነው የምንፈራው ትምርት ቤት፤ ሊድሩኝ ሲያስቡ እኔ ለትምርት ቤቱን ርዕሰ መምህርና የሴቶች ተጠሪ መምሕር አመልክቼ፣ ከጋብቻው ለማምለጥ ወሰንኩ። ከዚያም ወድያውኑ ሄጄ ተናገርኩ። ጋብቻው እንዲቋረጥልኝ ርዕሰ መምሕሩ ለቀበሌው ፖሊስ ተናገረና የመጀመርያውን ጋብቻ አቋረጠልኝ” ስትል ህብስት ገልጻለች።

የሴቶች ክበብ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተማሪዎች የሚመካከሩበት፤ መረጃ ለሚመለከታቸው የሕግና የአስተዳደር ባለስልጣናት፣ እንዲሁም ለመምሕራኖቻቸው የሚያደርሱበት ነው። የሴቶች ክበብ በተለይ በገጠር አካባቢዎች ከትምህርት የቀሩ ልጃገረዶችን፤ ወይንም የጋብቻ ወሬዎችን በሙሉ ሰብስቦ፤ በሕግ የሚያስጠይቀውን ባህል ለማስቀረት ይረዳል።

ያለ ዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት፤ የማኅበረሰቡን ግንዛቤ ማስጨበጥ ከባድ ፈተና መሆኑን የአካባቢው ባለስልጣናት ያስረዳሉ።

ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ቢሮዎች፣ የማኅበረሰብ ተቋማት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት(UNICEF) በዐስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ያለዕድሜ ጋብቻ እንዲቆም የጊዜ ገደብ አስቀምጠው በሥራ ተሰማርተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት መርሃ ግብርን የሚያስተባብሩት ዘምዘም ሽኩር፤ ያለ እድሜ ማግባት በተለይ በሴት ልጆች ኑሮ ላይ የሚያስከትለውን ተጽኖ ይዘረዝራሉ።

“አንደኛ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ። ስለዚህ ከቤት እመቤትነት ያለፈ የምጣኔ ሀብት ተሳትፎ አይኖራቸውም። ሌላኛው የጤና መዘዝ አለው። በተለይ በእርግዝና ጊዜ የህክምና አገልግሎት በቅርብ ካለማግኘትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ፤ ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርገዋል” በማለት ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከአምስት ልጃገረዶች አንዷ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሳይሞላት ትዳራለች። በሰሜን ምእራብ የጎንደር ከተማ ደግሞ ይሄ ብሔራዊ አኀዝ ከፍ ይላል።

የጎንደሯ ህብስት ታዲያ ጠያቂዋ ቢበዛም፤ ብትታጭም እስካሁን ባለመዳሯ ደስተኛ ናት። የህብስት እድል ግን ለጓደኞቿ እውን አልሆነም።

ህብስት ስለሁኔታው ስታስረዳ “አንደኛ እኛ አካባቢ፣ ሴት ልጅ ተምራ ሥራ ትይዛለች ብለው ሳይሆን ሴት ልጅ አግብታ ብዙ ዘሮችን ለማውጣት ዘመድ ለመፍጠር እያሉ ነበር እንጂ ሚያስቡት ሴት ልጅ ተምራ ትጠቅማለች ብለው አያስቡም”ብላለች።

ጎንደር ከተማ ውስጥ በግንዛቤ ማስጨበጫ በተዘጋጀ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ አብዛኛው ወጣት ወንዶች በታዳሚነት ተገኝተዋል። በዚህ ዝግጅት የተገኙ ወጣት ወንዶች ሴቶች ያለ ዕድሜያቸው እንዲዳሩ አይፈልጉም። ሰለሞን አሰፋ ከነዚህ ወጣቶች አንዱ ነው።

ሰለሞን ስለ ጉዳዩ ሲናገር “ምክንያቱም አቅማቸው የሚጠናው፣ ሰውነታቸው የሚበረታው እድሜያቸው ከፍ ባለ ቁጥር ነው። በዛ መካከል ደግሞ ትምሕርታቸውን የሚማሩበት ጊዜ አለ። መማር ስላለባቸው ከዐስራ ስምንት ዓመት በላይ ከሆኑ ግን ትምሕርታቸውን አጠናቀው የኔ የሚሉት ሰው ስለሚኖራቸው ከዛ በኋላ ትዳር ይመሰርታሉ" ብሎ ያስረዳል።

ህብስት አሁን የስመንተኛ ክፍል ተማሪ ናት። ወላጆቿ እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ትምህርቷን እንድትቀጥል እንደሚፈቅዱላት ተስፋ ታደርጋለች።

ወይዘሮ አበቤ አየለ ዐሥራ አራት ዓመቷ ነው። በዐሥራ ሦስት ዓመቷ አግብታለች። የስድስት ወር ልጅ አድርሳለች። ከጎንደር ከተማ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ትኖራለች። ልጅ በልጅነት አስቸጋሪ ነው ትላለች። የእድሜ እኩዮቿ ያባጯታል።

አበቤ ስለሁኔታው ስትናገር “በተለይ በአሁኑ ሰዓት መውለድ ከባድ እንደሆነ፣ ያለዕድሜዬ ስለወለድኩ ሽክሿኬ አለ፣ እንደዚ ሲያዩኝ ወልዳ ምናምን... በዛን ሰአት እኔ ሌላ ቦታ እወድቃለው፣ የሚሰማኝ ነገር አለ እርጉዝ እያለሁም ሌላ ነገር ሲሰማኝ ስለነበረ ይንሾኳሸኩብኝ ስለነረ…”ብላ ሐዘኗን አካፍላናለች።

አበቤ ትምህርቷን ለመቀጠል ተመዝግባ ነበር። ነገር ግን ከልጅ ጋር ትምሕርት አልሆነላትም፤ ሞግዚት ለመቅጠር አቅሟ አልፈቅድ ሲላት አቋረጠችው።

ዝርዝሩን ሔኖክ ሰማእግዜር ያቀርበዋል

በኢትዮጵያ ለአቅመ ሔዋን ሳይደርሱ የሚዳሩ ሴት ልጆች 4'17"
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:17 0:00

XS
SM
MD
LG