በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ተቃዋሚዎች እየታሠሩ መሆኑን ይናገራሉ


በኦሮሚያ ተቃዋሚዎች እየታሠሩ መሆኑን ይናገራሉ

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ቡድኖች «የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ ዓይነቱን ሕዝባዊ መነሳሳት ለመከላከል ያለመ ነው» ሲሉ በገለጹት መሠረት፥ ብዛት ያላቸው የፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪዎችን ይዞ አሥሯል።

ባልደረባችን ፒተር ኃይንላይን ከአዲስ አበባ እንደዘገበው፥ አፈሳው ያተኰረው ከሀገሪቱ ከሲሦ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በሚኖርበትና የፖለቲካው ስጋት ብርቱ በሆነበት በኦሮሚያ ክልል ነው።

የኦሮሞ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች እንደተናገሩት፥ በዚህ የፌዴራሉ ፖሊስ በጀመረው አፈሳ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ አንድ መቶ የሚሆኑ የፓርቲ አባሎቻቸው ተይዘው ታስረውባቸዋል።

አቶ በቀለ ገርባ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ ምክትል ሊቀመንበር እሥራቱ በኢትዮጵያ ትልቁ ግዛት ውስጥ በሚገኙ የተቃዋሚ ፖለቲካ እንቅስቃሴ መሪዎች መካከል ፍራቻ ፈጥሯል ብለዋል።

«ማንኛውም ቋንቋውን የሚናገርና የገዢው ፓርቲ አባል ያልሆነ ሰው፥ ተጠርጣሪ በመሆኑ ተይዞ ይታሠራል» ሲሉም አክለው አስረድተዋል።

የክልሉ ባለሥልጣናት ግን ክሱን ያስተባብላሉ።

«በሀገሪቱ ሕግና ሥርዓት አለ። ማንኛውም ሕጉን የሚጥስና የሕዝቡን እምነት አጉድሎ የተገኘ ተጠያቂ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የሚታሠር የለም» ያሉት ደግሞ ቃል አቀባዩ አቶ መስፍን አሰፋ ናቸው።

ሰሞኑን በኦሮሚያ ሰዎች በጅምላ እየተያዙ የሚታሠሩት፥ መንግሥት ባካባቢው ሀገሮች በተለይ በየመን የተቀሰቀሰው የፖለቲካ ሁከት እንዳሳሰበው በጠቆመበት ወቅት መሆኑ ይዘገባል።

ሁኔታው እንዳሳሰበውና መረበሹን የሚጠቁመው ሌላው ሃቅ ደግሞ፥ ሰሞኑን የቪኦኤን ሥርጭት ዳግም እያፈነ መሆኑ ታውቋል።

የጋዜጠኛ ፒተር ኃይንላይንን ዘገባ እዚህ ያድምጡ።

XS
SM
MD
LG