ኢቦላን ለመከላከል የሰለጠኑ ባለሙያዎች ከዛሬ ማክሰኞ፤ ነኀሴ 6/2006 ዓ.ም ጀምሮ ቦሌ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ ተመድበው ፍተሻ እያካሄዱ መሆኑ ተገለፀ፡፡
ለቫይረሱ ተጋልጧል ተብሎ የሚጠረጠር መንገደኛ ወይም ሰው ቢገኝ ለብቻ ነጥሎ የማቆያና የመንከባከቢያ ሥፍራ መመቻቸቱንም አንድ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥራ ኃላፊ ለቪኦኤ ገልፀዋል፡፡
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚመራ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ቫይረሱን የመከላከል፣ የማሳወቅና የጥንቃቄ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ቀድሞ ፓስተር፣ በኋላም የኢትዮጵያ የጤናና የሥነ-ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት እየተባለ ይጠራ የነበረውና በአዲሱ አደረጃጀት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተብሎ የተሰየመው ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አቤል የሻነህ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ስለ ኢቦላ ያውቃሉ ብሎ ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑን የገለፁት አቶ አቤል አሁን በተጀመረው ጥረት የሕብረተሰቡን ግንዛቤና ለማሳደግና ዕውቀት ለማዳበር በተለያዩ መንገዶች ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኤርትራ የመከላከያ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሯን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴሯ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ በሻባዪት ዶት ኮም ዌብ ሣይቱ ላይ ባሠፈረው ዘገባ መሠረት ስለቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶችና ስለበሽታው መገለጫ ምልክቶች ወቅታዊ መረጃዎችን ለሕዝብ ማውጣቱን አመልክቷል፡፡
የመከላከያ ክትባትና የሕክምና መድኃኒት ለሌለው ለኢቦላ ቫይረስ ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች፡- አስታማሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ሕመምተኞች ከሌሎች ተነጥለው ለብቻቸው የሚደረግላቸው እንክብካቤ ሠራተኞች ተመሣሣይ ምልክቶችን ባዩ ጊዜ ፈጥነው የጤና አገልግሎት እንዲጠይቁ የኤርትራ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መክሯል፡፡
የበሽታውን ሁኔታ የሚካታተል የባለሙያዎች ኮሚቴ ማዋቀሩን ሚኒስቴሩ አመልክቶ ሁሉም የጤና ተቋማት ተጋለጮች ቢገኙ ነጥሎ በማቆያ ሥፍራዎች ላይ ክትትል ማጠናከርን ጨምሮ በማሣወቅ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማሠራጨት ዓለምአቀፍ የመከላከያ እርምጃዎችን እንዲወስዱ አሳስቧል፡፡