በኤልኒኖ ምክንያት በተከሰተው ድርቅና በተከታታይ በቂ ዝናብ አለመዝነቡን ተከትሎ በኢትዮጵያ ከ10. 2 ሚሊዮን ዜጎች በላይ በድርቅ ምክንያት ለተረጂነት ተጋልጠዋል። የድርቅ ወራቱ እንዳለፈ ደግሞ በሀገሪቱ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሰሞኑን በተከሰተ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የመሬት መደርመስ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት እስከ አርብ ግንቦት አምስት ቀን ድረስ በአጠቃላይ የ92 ሰው ሕይወት ጠፍቷል። 86,000 ሰው ተፈናቅሏል። ከዚህ በኋላም ወደ 400 ሺህ ሰው ሊፈናቀል እንደሚችል እየተነገረ ነው።
በአፋር ክልል በጣለው በረዶ የቀላቀለ ዝናብ አምስት ሰው ሕይወት ጠፍቷል። በጅግጅጋ ከተማ በደረስ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ደግሞ የ23 ሰው ሕይወት መቅጠፉ ለአደጋው መከሰት የመጀመሪያው ነበ። በድሬደዋ ከተማ እና በአጎራባች ምስራቅ ሐረርጌ ከተሞች በዘነበ ዝናብ በደረሰ የጎርፍ አደጋ ሦስት ሰው ሕይወት ሲጠፋ ሁለት ሰው መቁሰሉ ይታወሳል። የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አቶ ምትኩ ካሳ አደጋው በስድስት ክልሎችና በሁለት ከተሞች የተከሰተ እንደኾነ ይናገራሉ።
በእነዚህ ቦታዎች በደረሰ የጎርፍ አደጋም የብዙ ሰው ሕይወት ጠፍቷል። በጎርፍ ከተወሰዱ ዜጎች በተጨማሪ በወላይታ ዞን የሚኖሩበት ቤት ላያቸው ላይ ተደርምሶባቸና በናዳ ተወስደው ሕይወታቸውን ያለፈ በርካታ ናቸው። በዚህ አካባቢ መሬቱ ከተደረመስ ከሁለት ቀናት በኋላ ከናዳው ውስጥ አንድ የሁለት ዓመት አዳጊ በሕይወት ተግኝቷል። እስካሁን በተከሰተው የጎርፍ አደጋ በወላይታ ዞን የጠፋው የ39 ሰዎች ሕይወት ትልቁን ቁጥር እንደሚይዝም አቶ ምትኩ ነግረውኛል።
የወላይታ ዞን ፖሊስ መምሪያ ረዳት ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ ማሞ ከእነዚህ 39 ሟቾች ውስጥ ነፍሰጡር እና የአራት ዓመት ሕጻን ልጅ ጭምር እንዳለበት ይናገራሉ።የብሔራዊ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አቶ ምትኩ በበኩላቸው በወላይታ ዞን የሞቱትን ሠላሳ ዘጠኝ ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ 92 ሰው መሞቱን ይናገራሉ።
አቶ ምትኩ እንደሚሉት ጎርፉ በሰው ሕይወት ላይ ካደረሰው አደጋ በተጨማሪ ንብረት ፣ማሳ ላይ ያለ ሰበል፣ እቤት ውስጥ ያለ እህልና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት ስላለ በአጠቃላይ የደረሰውን ጉዳት ለማጥናት ከክልልና ከፌደራል ኮሚቴ ተቋቁሞ ጥናት እየተደረገ እንደሆን ተናግረዋል ነገር ግን እስከዛው ድረስ በደረሳቸው ሪፖርት መሠረት ከፍተኛ ማሳ የወደመበት አካባቢ ያሉትን አስረድተዋል።
አቶ ምትኩ ካሳ ጎርፉ ከማጋጠሙ በፊት ከፍተኛ ጥንቃቄ በመደረጉ ምክንያት የሟቾች ቁጥር መቀነሱን ይናገራሉ። አደጋው ካጋጠመም በኋላ ሰዎችን ከሞት አደጋ ለመታደግ ጥረት እንደሚደርግ ገልጸዋል። ለዚህም በአፋር ክልል አሚባራ አካባቢ ቴሩ በደረሰው የጎርፍ መጥለቀለቅ በውሃ የተከበቡ ሰዎችን ለማትረፍ በሂሊኮፕተር ጭምር ተጠቅመው ሰዎችን ማትረፋቸውን ተናግረዋል። በአደጋው ንብረታቸውን ላጡ ተፈናቃዮች መልሶ ለማቋቋም እርዳታ እንደሚሰጥም ጨምረው ገለፀዋል።
በቀጣይም ከኤሊኖ ተቃራኒ የኾነው "ለሚና” እየተከሰተ በመኾኑ እስከ ጥቅምት ድረስ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚኖር ገልጸዋል። በዚህ አደጋም እስከ 400 ሺሕ ሰው ከቀየው ሊፈናቀል እንዲሁም ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ ይኖራል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመቃል። ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች በወንዝ ዳር የሚኖሩ ነዋሪዎች ከቦታቸው አስቀድመው እንዲነሱ እንደሚደርግም ገልፀዋል።