በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ያለፈው ዓመት እንቅስቃሴ


የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ዓመት ከቀደሙት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የምግብ መጠን ከታዳጊ አገሮች እንደሸመተና ለድርጅቱ ምግብ ከሸጡ 96 አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ ባለፈው የአውሮፓዊያን 2010 ዓመተ ምህረት በ1.25 ቢሊዮን ዶላር 32 ሚሊዮን ኩንታል እንደሸመተ ገልጿል። መጠኑ ከቀደመው የአውሮፓዊያን 2009 በ22 በመቶ በዋጋ ደግሞ በ30 በመቶ እንደጨመረና ሰማኒያ በመቶው ከታዳጊ አገሮች እንደተሸመተ በአፍሪቃ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ፒተር ስሜርዶን ከናይሮቢ በስልክ ገልፀውልናል።

በአውሮፓዊያን የዘመን አቆጣጠር በ2010 ከተሸመተው አጠቃላይ ምግብ 83 በመቶው በሌላ አነጋገር 26 ሚሊዮን ኩንታል የተሸመተው ከታዳጊ አገሮች መሆኑን ስሜርዶን ጠቁመው ይህ ኢትዮጵያን፣ ቪየትናምና ጓቲማላን ጨምሮ ከ ዘጠና ስድስት አገሮች የተሸመተ ምግብ በፓኪስታን በጎርፍ ማዕበል የተፈናቀሉትን፣ በሄይቲ በርዕደ ምድር የተጠቁትን፣ በአፍሪቃ ከሰሃራ በረሃ በስተደቡብ ባሉ አገሮች በድርቅ፣ እንዲሁም በሌሎች የዓለም ክፍሎች በተፈጥሮ መቅሰፍት የተጎዱትን ህዝቦች ለመታደግ እርዳታ መዋሉን አመልክተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ያለም ምግብ ፕሮግራም ከታዳጊ አገሮች የሚሸምተው ምግብ መጠን ዘንድሮ በ22 በመቶ እንዲጨምር የረዳው ድርጅቱ ባለፈው ዓመት ያገኘው እርዳታ ከምግብ ይልቅ ገንዘብ በመሆኑ እንደሆነ ስሜርዶን አመልክተዋል፡፡

ድርጅቱ ጊዜና ገንዘብ ለመቆጠብ እንደሚጥርም ገልፀዋል።

አብዛኛውን ጊዜ ምግብ ለመሸመት የሚጥሩት አስቸኳይ እርዳታ ከሚፈለግባቸው አካባቢዎች መሆኑን ቃልአቀባዩ አመልክተው በዚህ ዘዴ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ ምግብ መሸመት እንደሚችሉ፣ የማጓጓዣ ወጪ እንደሚቀንሱ፣ ምግቡን በፍጥነት በማድረስም በርካታ ሰዎች መመገብ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

እርምጃው በታዳጊ አገሮች እርሻ ላይ መዋለ ንዋይ በማፍሰስ ኢኮኖሚያቸውን ለማጠናከር እንደሆነ ገልፀው ይህ "ሸመታ ለእድገት" የተባለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

"ሰብላቸውን አንድነት ሰብስበው ከሚሸጡልን አነሰተኛ ገበሬዎች ነው እህሉን የምንሸምተው" የሚሉት ስሜርዶን አሠራሩ አነስተኛ ገበሬዎች ምርታቸውን በንፅህና ጠብቀው ምርጥ እህል ለገበያ ማቅረብ እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ፡፡

"በአፍሪቃ በተለይ እነዚህ አነስተኛ ገበሬዎች ድርቅ ወይም ሌላ የተፈጥሮ ችግር በመጣ ቁጥር ለአደጋና ለረሃብ የሚጋለጡ ናቸው። በዚህ ፕሮግራም እርዳታ ግን እንዲህ ዓይነቱን ቀውስ ለመቋቋም አነስተኛም ቢሆን ተቀማጭ ገቢ ይኖራቸዋል።" ብለዋል የዓለም የምግብ ፕሮግራሙ ቃልአቀባይ ስሜርዶን፡፡

ኢትዮጵያ በቅርቡ 2.8 ሚሊዮን ዜጎች የምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸው መግለጿን የዓለም ምግብ ፕሮግራም የአፍሪቃ አህጉር ቃል አቀባይ ፒተር ስሜርዶን አስታውሰው ምግብ ከተትረፍረፈባቸው አካባቢዎች እጥረት ወዳለባቸው ለማድረስ መንግሥት የዓለም አቀፉ ማኅበረስብ እርዳታ ስለሚያስፈልገው ከአነስተኛ ገበሬዎች እየሸመተ መልሶ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይሰጣል ብለዋል።

ስሜርዶን አክለውም ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ 88 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ምግብ መሸመታቸውን ገልፀው ይህም ባለፈው ዓመት ምግብ በብዛት ከሸመቱባቸው ቀዳሚዎቹ 15 አገሮች 7.07 በመቶውን የሚይዝ እንደሆነ አመልክተዋል። የሚሸምቱት የእህል ዓይነቶች በጣም የተለያዩ ቢሆኑም የሚበዛው ግን ማሽላና በቆሎ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከኤርትራ ምግብ ይሸምት እንደሆን ተጠይቀው "በሃገሪቱ ውስጥ ምንም እንቅስቃሴ ስለሌለን ከኤርትራ አንሸምትም" ብለዋል።

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG