የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት በትግራይ ውስጥ እየተባባሰ ባለው ጦርነት መካከል የሚገኙ ወደ 24ሺ የሚሆኑ የኤርትራውያን ስደተኞች ትልቅ አደጋ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ማይጸብሪ አካባቢ እየተካሄደ ያለው ውጊያ እየተጠናከረ በመምጣቱ በማይ አኒ እና አዲ ኻሩሽ በተባሉ የመጠለያ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች ደህንነት አደጋ ላይ ናቸው፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ድርጅት እኤአ ከሀምሌ 14 ጀምሮ ወደ መጠለያ ጣቢያዎች ዘንድም ለመድረስ አለመቻሉን ገልጿል፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስደተኞች ያሉበት ሁኔታ እጅግ እየከፋ መመጣቱንም አስታውቋል፡፡
የ UNHCR ቃለ አቀባይ ባርባራ ባሎች እንደሚሉ ታጣቂ ኃይሎች ወደ ካምፑ ውስጥ ዘልቀው ገብተዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ኤርትራውያኑ ስደተኞች በማቋርጥ ፍርሃት ውስጥ ናቸው፡፡ እርዳታዎችን እንዳያገኙ የተቆረጡ ሲሆን ማስፈራሪያዎችና ዛቻዎችም እየደረሱባቸው እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
ከማይ አኒ ካምፕ ውስጥ ቢያንስ አንድ ስደተኛ ካምፕ ውስጥ ባለ አንድ ታጣቂ መገደሉን የሚገልጽ አስደንጋጭ ዜና ከታመነ ምንጭ ሰምተናል፡፡ ሀምሌ 14 ከተገደለው አንድ ሰደተኛ ሞት በኋላ ይህኸኛው ተጨማሪ መሆኑ ነው፡፡
ባሎች እንደሚሉት ለግድያው ተጠያቂ የሚሆኑት የትኞቹ የታጣቂ ቡድኖች እንደሆኑ አያዉቁም፡፡ ይሁን እንጂ ግን የሳቸው ድርጅት በሁለቱ ካምፖች ውስጥ የሚገኙ ታጣቂዎች ድርጊቱን መፈጸማቸውን ከታመኑ ምንጮች የደረሱ መረጃዎች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
ቃለ አቀባዩ አክለውም UNHCR በአካባቢው ላሉ ባለሥልጣናትና ለኢትዮጵያ የስደተኞች ድርጅት ለስደተኞቹ ደህንነት ዋስትና እንዲሰጡና እርዳታ ሰጭዎች ወደ ካምፖቹ እንዲገቡ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ገልጸዋል፡፡ የኤርትራ ስደተኞ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ምንም እርዳታ ያላገኙ መሆኑም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
“በሁኔታው የታገቱ ስደተኞች አስቸኳይ የህይወት አድን ድጋፍ ይፈልጋሉ፡፡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እያለቀ ነው፡፡ ምንም ዐይነት የጤና አጠባበቅ አገልግሎት የለም ረሀብ ያፈጠጠ ትክክለኛ አደጋ ሆኗል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጣቸው የምግብ እርዳታ ባላፈው ሰነኢ ለአንድ ወር ብቻ የተሰጣቸው እርዳታ ነው፡፡”
ባሎች በቅርቡ በስተምስራቅ ትግራይ በአፋር ክልል በተደረገ ውጊያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተፈናቀሉ ሲሆን ከ እነዚህ ውስጥ 55ሺ የሚደርሱ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡ እየተባባሰ የመጣው ውጊያ ደህንነታቸው አሳሳቢ የሆኑ ስደተኞች ባሉበት አካባቢ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የቪኦኤ ዘጋቢ ሊዛ ሽላይን ከጄኔቭ ከላከችው ዘገባ የተወሰደ፡፡