በሰሜን ጎንደር ዞን ከሚገኘው የአለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ አምስት ኤርትራዊያን ስደተኞች በአማራ ክልል የጸጥታ ሓይሎች መታሰራቸውን ቪኦኤ ያነጋገራቸው እማኞች ተናገሩ፡፡ ኤርትራዊያኑ ስደተኞች ከአለምዋጭ ካምፕ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዳባት ከተማ በሚገኝ እስር ቤት ታስረው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለደኅንነቱ ሲባል ስሙ የማይገለጸው ለታሰሩት ስደተኞች ቅርብ የኾነ ምንጭ እንዳለው ስደተኞቹ የተያዙት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ዳባት ከተማ ከሚገኘው የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሲወጡ ነው፡፡ መረጃዎቻቸውን የሚመለከቱ ጉዳዮች ለማጣራት በሚል ወደ ጽሕፈት ቤቱ ተጠርተው ሲወጡ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር አውሏቸዋል ሲል ምንጩ አክሎ አመልክቷል፡፡
ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የማይጠቀስ የሌላ ታሳሪ ባለቤት ለቪኦኤ በሰጠችው ቃል ባለቤቷ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዳባት ውስጥ መታሰሩን ገልጻ በምን ምክንያት እንደታሰረ ለማወቅ ያደረገችው ሙከራ እንዳልተሳካ ተናግራለች፡፡
የእስር ቤቱ ሁኔታ አስከፊ መሆኑን የተናገረው ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ስደተኛ በበኩሉ ኢስማኢል አህመድ፣ ፍስሃዬ ኪዳኔ፣ አብዱ አህመዲን፣ መሰረት ገብረስላሴና አታክልቲ ሃይሌ የተባሉ እስረኞች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አመልክቷል፡፡
አለምዋጭ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ የሚገኝበት የጭላ ቀበሌ አስተዳዳሪ ምናለ ግብነህ ስለስደተኞቹ እስር መረጃ የለኝም ብለዋል፡፡ ሆኖም በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር እና ዝርፊያ የመሳሰሉ ወንጀሎች ውስጥ በመሳተፍ ወይም ከአማራ ክልል ለመውጣት በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲካሄድ በመቀስቀስ ተግባር የሚወነጀሉ አንዳንድ ስደተኞች አሉ ብለዋል። የታሰሩት ስደተኞች ከጠቀሷቸው አድራጎቶች ጋራ ግንኙነት አላቸው ወይ? የሚለውን ባለሥልጣኑ ማረጋገጭ አልሰጡም፡፡
የመንግሥታቱ ድርጅት የስድተኞች ኮሚሽን (ዩ ኤን ኤች ሲ አር) በበኩሉ በጽሑፍ በሰጠው ምላሽ "ከአለምዋጭ ካምፕ አምስት ስደተኞች ለስድተኞች እና ለጥገኝነት ጠያቂዎች ያልተፈቀደ እንቅስቃሴ በማድረግ ተወንጅለው መታሰራቸውን እናውቃለን” ብሏል፡፡ ትክክለኛ የፍርድ ሂደት እና የሕግ ጥበቃ እንዲረጋገጥላቸው የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎትን መጠየቁን ገልጾ ሂደቱን በቅርበት በመከታተል ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡
መድረክ / ፎረም