ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በማባባስ እና የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግረው በተፈፀሙ ወንጀሎች በዩናይትድ ስቴትስ ዓመታዊ የሰብአዊ መብት ሪፖርት የተወቀስች ኤርትራ፣ ወቀሳውን አጣጣለች።
የዩናዩትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሃገራትን የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በተመለከተ ባለፈው ሳምንት ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት ላይ በኤርትራም ስላለው የመብት አያይዝ ሁኔታ ያካተተውን ሪፖርት በተመለከተ ኤርትራ በሰጠችው ምላሽ፣ “የተለመደና ለረጅም ጊዜ ተአማኒነት ያጣ የሃሰት ክስ ነው” ብላለች።
ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በወጣው መግለጫ ምላሽ የሰጠው የኤርትራ መንግሥት፣ “አሜሪካ ቀድሞውንም በሰብአዊ እና የመንግሥት አስተዳደር ሌላውን ዓለም ልትሰብክ ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ መብት አላት?” ሲል ጠይቋል።
በኢትዮጵያ ስላለውና በመንግሥት ላይ ስለሚካሄደው አመጽና ጦርነት ሪፖርቱ በስፋት መዘረዘሩ፣ አሜሪካ የሚያሳስባት የኤርትራ ሕዝብ ደህንነትና የቀጠናው ሰላምና መርገጋጋት እንዳልሆነ አሳይቷል”
ባለፈው ሳምንት የወጣው የአሜሪካው ዓመታዊ የሃገራት የሰብአዊ መብቶች አያያዝ በሚገመግመው ሪፖርት፣ ኤርትራ ከቀደሙት ሪፖርቶች አንጻር የተለየ ለውጥ እንደሌለ አስፍሯል። የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች ባለፈው መጋቢት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ግጭት የጦር ወንጀሎችን ጨምሮ ግድያ፣ መድፈርና ሌሎች የጾታ ጥቃቶች መፈጸማቸውን፤ በሃገሪቱ መንግሥት የግዳጅ መሰወር፣ ሰቆቃ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ኢሰብአዊ የሆነ አያያዝ፣ አስቸጋሪና ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል የእስር ቤት ሁኔታ፣ በዘፈቀደ መያዝና ማሰር፣ የፍትህ አካላት ገለልተኛ አለመሆን፣ በፖለቲካ ምክንያት መታገት፣ በሌሎች ሀገራት በሚገኙ ኤርትራውያን ላይ የሚፈጸም ጭቆና፣ እና ሌሎችንም የመብት ጥሰቶች ሲል የገለፃቸውን በዝርዝር አስቀምጧል። የኤርትራ ኢምባሲ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፣ "የሪፖርቱን ይዘት፣ አሠራር፣ ትርክት እና ድብቅ ገፊ ምክንያት በማያሻማ መንገድ ይቃወማል” ብሏል። “ሪፖርቱ ከተለመደውና በኤርትራ ላይ ከሚሰነዘረው መራር ወቀሳ ምንም የተለየ ነገር የለውም” ሲልም አክሏል።
“በኢትዮጵያ ስላለውና በመንግሥት ላይ ስለሚካሄደው አመጽና ጦርነት ሪፖርቱ በስፋት መዘረዘሩ፣ አሜሪካ የሚያሳስባት የኤርትራ ሕዝብ ደህንነትና የቀጠናው ሰላምና መርገጋጋት እንዳልሆነ አሳይቷል” ብሏል።
“ለጂዮ ፖለቲካ ጥቅም ሲባል የኤርትራን የማይገረሰሥ መብት አደጋ ላይ በሚጥልና በቀጠናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ የባይደን አስተዳደርም ለዓመታት የነበረውን የአሜሪካ አቋም ዋና ጉዳዩ አድርጎ ቀጥሎበታል” ሲል አክሏል መግለጫው።
መድረክ / ፎረም