በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

«አገርህስ እምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?» - የኤርትራ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት


አሥመራ ቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊካዊት ካቴድራል
አሥመራ ቅዱስ ዮሴፍ ካቶሊካዊት ካቴድራል

የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን አራት ጳጳሶች የኤርትራዊያን ወጣቶች እልቂትና የሚታየው ፍልሰት ያሳሰባቸው መሆኑን ገለፁ።


የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን አራት ጳጳሶች የኤርትራዊያን ወጣቶች እልቂትና የሚታየው ፍልሰት ያሳሰባቸው መሆኑን ገለፁ።

አራቱ ጳጳሳት አቡነ መንግሥተ-አብ ተስፋማርያም ዘመንበረ አሥመራ፣ አቡነ ቶማስ ኡስማን ዘመንበረ ባረንቱ፣ አቡነ ኪዳነ የዕብዮ ዘመንበረ ከረን እና አቡነ ፍቅረማርያም ሐጎስ ዘመንበረ ሰገነይቲ ሲሆኑ ማሳሰቢያውን የፃፉትም «ወንድምህ ወደ የት አለ?» በሚል ርዕስ ባሠራጩት ፅሁፍ መሆኑ ታውቋል።

ጳጳሳቱ በዚሁ መልዕክታቸው ለውጥ ፈላጊው ወጣት የባሕር ሲሳይና የዘመናችን የሰው ንግድ አውሬዎች ቀለብ እስከመሆን መድረሱና ስደትን በተመለከተም በወጣቱ ላይ ‘ሕይወቴ የሚሻሻለው ውጪ ከሄድኩኝ ብቻ ነው’ የሚል ስሜት ማደሩ እንዳሳሰባቸው አመልክተዋል።

“ሰላም፣ ፍትህ፣ ሠርቶ መኖርና ሳይፈሩ መናገር ባለበት አገር፣ ከመሰደድ ይልቅ፣ የተሰደደው ይመለሳል” ብለዋል አባቶቹ።

ኤርትራ ውስጥ በነፃነት መወያየት መታጣቱና መረጃ ያለማግኘቱ ሰዉ ተንሾካሹኮ እንዲነጋገር፣ የሀሜትና የግዴለሸነት ባህል እንዲያንሠራራ ማድረጉንም በደብዳቤያቸው ጠቅሰዋል።

የአባቶቹ ደብዳቤ “ዛሬ ኤርትራ ውስጥ ‘በህግ አምላክ!’ የሚለው ባህል ስለጠፋ ይሆን ሙስና የበረከተው?” ብሎ ይጠይቅና “ለፍትህ፣ ለርትዕ፣ ለህግ የበላይነት፣ ለእውነት መቆም፣ ሁሉም የሚፈልገው ስለሆነ ትኩረት ሊያገኝ ይገባዋል” በማለት ጥሪ ያደርጋሉ።

ኤርትራዊያኑ የካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን ጳጳሳት «ሐዋርያዊ መልዕክት» ባሉት በዚሁ ፅሁፋቸው “ወንድምህ ወደ የት አለ?!” ስንባል “እኔ የወንድሜ ጠባቂ ነኝን?” በማለት ለጥያቄው አጭር መልስ ከመስጠት ይልቅ ጥያቄውን ሰፋ አድርገን «አገርህስ እምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?» እስከማለት መኬድ እንዳለበት አሳስበዋል።
XS
SM
MD
LG