በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ውኃ አልባው ባሕር


እሳተ-ገሞራና የስንጥቅ መፈጠር፣ ሣይንቲስቶች እንደሚሉት፣ መላውን ስምጥ ሸለቆ በሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ ወደ ግዙፍ ባሕርነት ሊለውጠው ይችላል፤ ሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከታንዛኒያ የሚተርፈው የየብስ አካል አዲስ ግዙፍ ደሴት ሊሆን ይችላል፡፡
እሳተ-ገሞራና የስንጥቅ መፈጠር፣ ሣይንቲስቶች እንደሚሉት፣ መላውን ስምጥ ሸለቆ በሦስት መቶ ዓመታት ውስጥ ወደ ግዙፍ ባሕርነት ሊለውጠው ይችላል፤ ሶማሊያ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያና ከታንዛኒያ የሚተርፈው የየብስ አካል አዲስ ግዙፍ ደሴት ሊሆን ይችላል፡፡

የደናክል ረባዳማ አካባቢዎች ነውጥና ንቅናቄ መስተዋል ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

የሰሜናዊው አፍሪካ ከርሰ ምድር እንቅስቃሴ ቀስ በቀስ እየተንፏቀቀ አህጉሪቱን አንድ ቀን ወደ መሰንጠቅ ሊወስዷት እንደሆነ የቅርብ አጥኚዎቹ እየተናገሩ ነው፡፡

በተለይ የአፋሮቹ እሳተ-ገሞራዎች የሚተፉት የቀለጠ ዐለት ፍሳሽ በውቅያኖሶቹ ወለል ላይ የሚታየውን ዓይነት ማግማ እንደሚመስል የሚያመላክቱት እነዚህ አጥኚዎች ያንን ሃገር ወደፊትም የሚተኛበት የባሕሩ ውኃ እንደሚሆን ይተነብያሉ፡፡

በአፋር ስሙ ገንኖ የሚነሣው የኤርታአሌ እሳተ-ገሞራ ለመጨረሻ ጊዜ ከፈነዳ አሠርት ዓመታት አልፈዋል፡፡ ሆኖም ኤርታአሌ ጨርሶ አልተኛም፡፡ አናቱ ላይ ያለው ብርማ የቅልጥ የአለት ኩሬ እንደተንፈቀፈቀ ይኖራል፡፡

ባለፈው ሕዳር ውስጥ አርታአሌ አገርሽቶበት እንደገና መተኮስና እንደገና መገንፈል መጀመሩ ተሰማ፡፡

በኒው ዮርክ ሮቸስተር ዩኒቨርሲቲ የጂዖ ፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ርዕደ-ምድርና እሳተ-ገሞራ እንቅስቃሴ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩትና የሚመራመሩት ዶ/ር ሲንቲያ አቢንገር በምሥራቅ አፍሪካ የአዲስ ባሕር መፈጠርን የተፈጥሮ ሂደት እያስተዋሉ ነው፡፡

ክልሉ በሙሉ ዕድሜው የከርሰ-ምድር እንቅስቃሴ ተለይቶት ባያውቅም በቅርብ ዓመታት የሚታየው ዓይነት ክስተት ግን እጅግ የፈጠነ መሆኑን አካባቢውን የሚያጠኑ ጠቢባን ይናገራሉ፡፡ “አፍሪካ በጂዖሎጂ ማለትም በከርሰ ምድር ጥናት እምብዛም ተዘውትሮ በማይስተዋል ሁኔታ ለሁለት እየተሰነጠቀች ነው፡፡” ይላሉ፡፡

እንዲያውም ቀይ ባሕርንና አደን ባሕረ-ሠላጤን ወደ በረሃው ከመገልበጥ በደረታቸው ያቆሙት ከፍታቸው ከሃያ አምስት ሜትር ያልበለጠ ገሞራ ወለድ ኮረብታዎች መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡

የበረሃው ምድር እየተሰነጠቀና ክፍተቱ በፍጥነት እየሰፋ መሬቱ እየተራራቀ ነው፤ እሳተ-ገሞራዎቹ መረጋጋት አጥተዋል፡፡ የባሕሩ ውኃ በመሬቱ ላይ የተፈጠረውን የመሰንጠቅ አጋጣሚ ተከትሎ እየተሠረቀ ይፈልቃል፡፡ የተጠማው ምድረ በዳ እነሆ የጨዋማው ውኃ መተኛ ሊሆን ነው፡፡

የዛሬውን ዐረቢያ ልሣነ-ምድር ከአፍሪካ ምድር ፈልቅቆ በማሸሽ ቀይ ባሕርንና አደን ባሕረ-ሠላጤን ከፈጠረው ከሚሊዮኖች ዓመታት በፊት ከተከሰተው የሰሜናዊ አፍሪካ አውራጃ የመጀመሪያው መሠንጠቅ በኋላ ያጋጠመው በገፀ-ምድር ላይ የታየ የከርሰ-ምድር ክስተት ከቀይ ባሕር ዳርቻዎች አንስቶ ወደ ደቡብ የተዘረጋው፣ ታንዛኒያን ዘልቆ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ የገባው የታላቁ ስምጥ ሸለቆ መፈጠር ነበር፡፡

“ወደፊት በሚሊዮኖች ዓመታት ይህ የስምጥ ሸለቆ ሃገር በሙሉ የውኃ መተኛ ይሆናል፤” ይሉ ነበር ተመራማሪዎቹ ቀድሞ በነበራቸው ግምት፡፡ ዛሬ ግን ያ ሃሣብ ተለውጧል፡፡ ጊዜው ያንን ያህል የመርዘሙን ጉዳይ አሁን አሁን ክኻሊያኑ (ኤክስፐርቶቹ) ይጠራጠራሉ፡፡ በተለይ በስምጥ ሸለቆ የሰሜን አናት ላይ የሚገኘው ደንከል ረባዳ መሬቶች ከታሰበው ጊዜ በፈጠነ ሁኔታ የባሕር ወለል ይሆናሉ፡፡ መቶ? ሺህ? መቶ ሺህ ዓመት? ተመራማሪዎቹ ለጊዜው ቁርጥ ቁጥር አይጠሩም፡፡ ብቻ ሚሊዮን የመሆኑን ጉዳይ ግን አንዳንዶቹ በምቾት አይቀበሉትም፡፡

ከእነዚያ ሃያ አምስት ሜትር ብቻ ከፍታ ካላቸው ኮረብታዎች ጀርባ የተንጣለለው ምድር በፈጠነ ሁኔታ እየሰጠመ ወይም በፍጥነት ከባሕር ጠለል ልክ እየወረደ ነው፡፡ በአንድ በኩል፣ በመሬቱ ገፅታ ላይ የሚታየው ጨዋማ ተፈጥሮ ባሕሩ ሥር ሥሩን እየሠረገ እንደነበር ያመላክታል፡፡ ያኔ ግን እሳተ-ገሞራዎቹ ተገለበጡና ቅልጡ ግንፍላቸው ጠረፉ ላይ ሲፈስ እንደ ግድብ ተኮልኩለው የባሕሩን ውኃ ወደ መሬቱ ከመገልበጥ ያቆሙትን ከፍታዎች ፈጠረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚያ በጨው ምጣዶች የተሞሉ በሜዳማው ሃገር ላይ የተኙ ድርብርቦችና የቅልጥ አለት አካላት አካባቢው ከዚህ ቀደም ከባሕር ሥር እንደነበር፣ ኮረብታዎቹ ሲፈጠሩ ከባሕሩ ተለይቶ የተከተረው ውኃ በተጋነነው የአካባቢው ሙቀት ሣቢያ መትነኑንና መሬቱ መድረቁን እንደሚጠቁሙ ፕሮፌሰር አቢንገር አመልክተዋል፡፡ በዚህ ሣቢያ ዛሬ ክልሉን “ውኃ የለሹ ውቅያኖስ” እያሉ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይጠሩታል፡፡ (ይቀጥላል)

ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG