በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የግብፅ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ምቾት አይሰጥም - ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ


ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ስለግብፅ
ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ስለግብፅ

የግብፅ ሁኔታ ከጎረቤት አንፃር ሲታይ በጣም የሚያሣዝን ነው ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ አመለከቱ፡፡
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:33 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

የግብፅ ሁኔታ ከጎረቤት አንፃር ሲታይ በጣም የሚያሣዝን ነው ሲሉ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ አመለከቱ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፊሰር እና በናይል ጉዳይ ተመራማሪው ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ለቪኦኤ በሰጡት ትንታኔ በሁለት የፖለቲካ ጎራ ተከፍለው መገዳደልና የፀጥታ መደፍረስ በሃገሪቱ መስፈኑ በጣም የሚያሣዝን ሆኖ ያገኙት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

“ሙስሊም ወንድማማችነት የፈለጉትን አላገኙም፣ የሚፈልጉትንም አያገኙም፤ ወታደሮቹም ከያዙት አቋም የሚነቃነቁ አይመስልም” የሚሉት ዶ/ር ያዕቆብ አርሣኖ ለሁለቱም ወገኖች የሚሻላቸው ወደ መቻቻልና ዕርቅ ተመልሰው ሃገራቸውን መገንባት መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያን በሚመለከት አሁን ይህንን ያህል የጎላ ሥጋትና አደጋ እንደማይታያቸው ዶ/ር ያዕቆብ አመልክተው እዚያ ያለው ብጥብጥ ለዲፕሎማሲም ሆነ ለግንኙነት አስቸጋሪ ስለሚሆን ካይሮ ላይ ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ምቾት ይሰማታል ብለው እንደማያስቡ አስረድተዋል፡፡

“የተበጠበጠና ችግር ውስጥ ያለ ጎረቤት ምንጊዜም ቢሆን የተረጋጋ ሊሆን ስለማይችል ሃሣቡም ሆነ መጠኑ ምን እንደሆነ አይታወቅም” ብለዋል ዶ/ ያዕቆብ አርሳኖ፡፡

ዩናይትድ ስቴትስም ብትሆን ሁኔታው ለጊዜው ስላሳሰባት ከግብፅ ጋር ለማካሄድ አቅዳው የነበረውን የጋራ የጦር ልምምዷን ታቋርጥ እንጂ በአካባቢው ግብፅን ሊተካ የሚችል ወዳጅ ልታገኝ ስለማትችል ግንኙነቷንና እርዳታዋን ጨርሶ ትዘጋለች ብለው እንደማያስቡ ገልፀዋል፡፡

የአሜሪካ ከዚያ መራቅ ወይም መሻከር በአካባቢው የእሥራኤልን ደኅንነት አደጋ ላይ እንዲጥልም ሆነ የኢራንን ማየል እንዲያስከትል፤ ሩሲያና ቻይናም በሚፈጠረው ክፍተት እንዲገቡ እንደማትፈልግና እንደማትፈቅድም ያላቸውን ሃሣብ ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ
ዶ/ር ያዕቆብ አርሳኖ

ሙሉውን ቃለምልልስ ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG