በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኪረሙ ወረዳ 8 አርሶ አደሮች በታጣቂዎች እንደተገደሉ የኮምዩኒኬሽንስ ጽ/ቤቱ አስታወቀ


በኪረሙ ወረዳ 8 አርሶ አደሮች በታጣቂዎች እንደተገደሉ የኮምዩኒኬሽንስ ጽ/ቤቱ አስታወቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:56 0:00

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ፣ ባለፈው ሳምንት ውስጥ፣ ስምንት አርሶ አደሮች፣ በታጣቂዎች እንደተገደሉ፣ የወረዳው ኮምዩኒኬሽንስ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ ጅሬኛ ሄርጳ፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታወቁ።

የወረዳው ኮምዩኒኬሽንስ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ እና የተጎጂ ቤተሰብ አባላት እንደሆኑ የገለጹ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ጥቃቱ የተፈጸመው፣ “ጽንፈኛ” ሲሉ በጠሯቸው የዐማራ ታጣቂዎች እንደሆነ ገልጸዋል። የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ መሆናቸውን የገለጹና መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት አቶ ኡመር ሽፋው፣ ኪረሙ ላይ ጥቃት የሚደርሰው በዐማራ ተወላጆች ላይ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ(ኢሰመጉ)፣ በጉዳዩ ላይ ክትትል እያደረገ እንደሆነ ገልጿል።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ዋስት ቀበሌ፣ ነዋሪ እንደሆኑ በስልክ የገለጹ፣ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ ባለፈው ሳምንት፣ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም፣ “የዐማራ ጽንፈኞች” ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች፣ ከገደሏቸው ንጹሐን ዜጎች መካከል፣ አማቻቸው እንደሚገኙበት፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ተናግረዋል።

“አማቼ ነው የተጎዳብኝ። በየነ በከሬ ጉዳ ይባላሉ። በእርሻ ላይ እያለን፣ እነዚኽ ሰዎች(በባጊን ቀበሌ የተወለዱ እና እነርሱን ተገን ያደረጉ ከዐማራ ክልል የመጡ በርካታ ቁጥር ያላቸው “የዐማራ ጽንፈኞች”) ወደ ቀበሌው በማምራት በከፈቱት ተኩስ፣ አማቼን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎችን ሲገደሉብን፣ 14 ሰዎችን ደግሞ አቆሰሉብን፡፡”

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ፣ ባለፈው ሳምንት ኀሙስ ማለዳ፣ በረት ሲጠብቁ አድረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ እያሉ፣ “ዐማርኛ ይናገራሉ ግን ማንነታቸውን አላውቅም” ሲሉ የገለጿቸው ታጣቂዎች፣ ተኩሰው እንዳቆሰሏቸውና በሕይወት ተርፈው በጊዳ ሕክምና ላይ እንደኾኑ በስልክ ገልጸዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች፣ ራሳቸውን ከሸማቂዎች ጥቃት ሲከላከሉ “ጽንፈኛ” እንደሚባሉ፣ ከዚኽ ቀደም ሲገልጹ ቆይተዋል። በአካባቢው “ሸኔ” ሲሉ በጠሩትና ጥቃቱን በተደጋጋሚ በሚያስተባብለው ታጣቂ ቡድን፣ ለበርካታ ጊዜ ጥቃት እንደሚደርስባቸው የተናገሩት ተወላጆቹ፣ ይህን ጥቃት ለመከላከል ራሳቸውን ሲያደራጁም “ፋኖ” የሚል ስያሜ እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። ይኹንና፣ ባለፈው ሳምንት፣ በኪረሙ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት፣ በአካባቢው የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆችን በስልክ አግኝተን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ በኩል፣ የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ መኾናቸውን የገለጹና መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት አቶ ኡመር ሽፋው፣ የዐማራ ተወላጆች ጥቃት ይደርስባቸዋል እንጂ፣ ጥቃት ያደርሳሉ፤ የሚል እምነት እንደሌላቸው፣ ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸው ነበር።

አሁን በኪረሙ ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት ጠይቀናቸው፤ ኪረሙ ቁጥራቸው የበዛ የዐማራ ተወላጆች የተገደሉባት አካባቢ ናት ብለዋል።

በዚህ ጉዳይ የተጠየቁት፣ የኪረሙ ወረዳ ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ጅሬኛ ሄርጳ፣ ሰኔ 8 2015 ዓ.ም. “የዐማራ ጽንፈኞች” ሲሉ የገለጿቸው ታጣቂዎች፣ “በኪረሙ ወረዳ ዋስት ቀበሌ ውስጥ፣ ስምንት ንጹሐን ሰዎችን ሲገድሉ፣ 13ቱን አቁስለዋል፤” ሲሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ታጣቂዎቹ፣ በበርካታ የወረዳው ቀበሌዎች ውስጥ፣ ካምፕ መሥርተው እንደሚገኙ የጠቀሱት ሓላፊው፣ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በፈጸሙት ጥቃት፣ ከ52ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ(ኢሰመጉ) ምክትል ዲሬክተር አቶ ተስፋዬ ገመቹ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ በኪረሙ ወረዳ፣ በንጹሐን ሰዎች ላይ ደረሰ ስለተባለው ጥቃት፣ በሌሎችም የክልሉ አካባቢዎች፣ በታጠቁ ኀይሎች ስለተፈጸሙ ጥቃቶች፣ ባለሙያዎቹ ክትትል እያደረጉ እንደኾኑ ገልጸው፣ በቅርቡ በዚኽ ጉዳይ፣ ኢሰመጉ መግለጫ ሊሰጥ እንደሚችል አመልክተዋል።

ባለፈው ሳምንትም፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ውስጥ፣ “የዐማራ ጽንፈኞች” ሲሉ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የሚጠሯቸው ታጣቂዎች፣ አምስት አርሶ አደሮችን መግደላቸውን የገለጹ ሲኾን፣ የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ አቶ ኡመር ሽፋው ግን፣ በአሁኑ ወቅት ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉት፣ የዐማራ ተወላጆች ናቸው፤ ሲሉ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ለአሜሪካ ድምፅ መግለጻቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG