በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሥራች ዣን ማሪ ለ ፔን አረፉ


የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሥራች ዣን ማሪ ለ ፔን
የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሥራች ዣን ማሪ ለ ፔን

በጸረ ስደተኛ እና በመድብለ ባሕላዊ ኅብረተሰብ ጠል ንግግራቸው የሚታወቁት የፈረንሳይ ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሥራች ዣን ማሪ ለ ፔን በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በከረረው ቀኝ ክንፍ አቋማቸው ብርቱ ደጋፊዎች የነበሯቸው እና በተቃዋሚዎቻቸው በስፋት ይወገዙ የነበሩት የብሔራዊ ግንባር ፓርቲው መሥራች ማረፋቸውን የፓርቲያቸው ፕሬዝደንት ዦርዳን ባርዴላ ዛሬ በኤክስ ገጻቸው ላይ አስታውቀዋል።

በፈረንሳይ ፖለቲካ እጅግ ከፋፋይ በኾነ አመለካከታቸው የሚታወቁት ለ ፔን በአይሁዶች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ማጣጣልን ጨምሮ አወዛጋቢ በሆኑ ንግግሮቻቸው በፍርድ ቤት በተደጋጋሚ የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል። ከፖለቲካ አጋሮቻቸውም ጋራ አቃቅሯቸዋል።

እ አ አ በ2002 ዓመተ ምሕረት ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እስከ ሁለተኛ ዙር ውድድር ዘልቀው የነበሩት ለ ፔን በኋላ ላይ ከሴት ልጃቸው ከማሪን ለ ፔን ጋር ተጣልተው ልጃቸው የፓርቲውን ስም ቀይረው አስወጥተዋቸዋል። ማሪን ከአባታቸው አክራሪ ገጽታ ራሳቸውን በማራቅ ፓርቲውን በፈረንሳይ ፖለቲካ እጅግ ጠንካራ ከሆኑ ኃይሎች መካከል አንዱ እንዳደረጉት አሶሲየትድ ፕሬስ ዘገባ አውስቷል።

ዣን ማሪ ለ ፔን ለፈረንሳይ የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ ኑሮ ችግሮች ተጠያቂ የሚያደርጓቸውን የእስልምና ኃይማኖትን እና ፈረንሳይ የሚኖሩ ሙስሊም ስደተኞች የፓርቲያቸው ግንባር ቀደም ዒላማዎች ማድረጋቸውን ዘገባው አክሏል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG