በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

“ከአሥመራ ፀሐይ በታች” ያለው የኤርትራዊው አርቲስት የበጎዎች ገጽ


“ከአሥመራ ፀሐይ በታች” ያለው የኤርትራዊው አርቲስት የበጎዎች ገጽ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:17 0:00

ኤርትራዊው ደራሲ እና ዲሬክተር ኤፍሬም ካህሳይ(ወዲ ዃዳ)፣ በሕዝብ ዘንድ በስፋት ከሚታወቅበት የፊልም እና ድራማ ሥራዎቹ ጋራ፣ “አብ ትሕቲ ጸሓይ አመራ” በሚል ርእስ፣ በፌስቡክ ገጹ በሚያሰፍራቸው ጽሑፎቹ፣ የብዙኀን አንባብያንን ቀልብ ለመሳብ ችሏል።

ኤፍሬም፣ በፌስቡክ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ በአሥመራ ከተማ ለሕዝብ በአበረከቱት መልካም ሥራ በሚታወሱ ታዋቂ ሰዎች በጎ ጎኖች ላይ ትኩረት ያደረገ ጽሑፍ ለተከታዮቹ እንደሚያጋራ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሯል።

የፊልም እና ድራማ ደራሲ እና ዲሬክተር ኤፍሬም ካሕሳይ(ወዲ ዃዳ)፣ በዋናነት ከሚታወቅበት የድራማ እና የፊልም ሥራዎቹ በተለየ፣ የታዋቂ እና አንጋፋ ሰዎችን ታሪክ፣ ባህል እና ሌሎችንም ለኣንባብያን ይጠቅማሉ የሚላቸውን ጽሑፎች፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ በመለጠፍ፣ ከ17ሺሕ በላይ ተከታዮችን ማፍራት የቻለ ኤርትራዊ አርቲስት ነው።

“አብ ትሕቲ ጸሓይ አስመራ” ማለት “ከአሥመራ ሓይ በታች” በሚል ርእስ፣ በፌስቡክ ገጹ ላይ የሚለጥፋቸው ጽሑፎች ዋና ዓላማ፣ በሕይወት ዘመናቸው በጎ ሥራ የሠሩ ሰዎችን ታሪክ በማጋራት፣ ወጣቱ ትውልድ እንዲማርበት በማሰብ እንደኾነ፣ ኤፍሬም ለአሜሪካ ድምፅ ተናግሯል።

“በበጎ ሥራቸው የሚታወቁ ሰዎችን ታሪክ ነው የምጽፈው። የሰዎችን መልካም ሰብእና እና በጎ ተግባር መናገር፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መልካም አስተሳሰብንና ጥሩ ስሜትን ለማሳደር ይረዳል።” የሚለው ኤፍሬም “በሌላ በኩል፣ ሁሉም ሰው የየራሱ በጎ ጎን እንዳለው ስለሚያሳይ፣ ለአገሪቱም ጥሩ ነው። ስለዚኽ፣ የግለሰቦቹ ግማሽ ጎን ላይ ኣተኩሬ ነው የምጽፈው፡፡” ብሎናል።

የአንድን ታዋቂ እና መልካም ሥራ የሠራ ሰው ታሪክ ለማጥናት፣ ከ3 እስከ 16 ሳምንታት ጊዜ እንደሚፈጅበት ኤፍሬም ይናገራል፡፡ የሰዎቹን ሐቀኛ እና ሙሉ መረጃ ለማሰባሰብ፥ ቤተሰቦቻቸውን፣ የቅርብ ወዳጆቻቸውንና የአካባቢ ነዋሪዎችን እንደሚያነጋጋግር ጠቅሷል፡፡

ባለታሪኮቹን ለመምረጥ ስለሚጠቀምበት መስፈርትም፣ ሲናገርም “ቅድሚያ የምሰጠው፣ ሰዎቹ የሚታወቁት በምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በሕዝቡ ዘንድ በአርኣያነት የሚታዩትንና በሥነ ምግባራቸው የሚወደዱትን፣ ለኅብረተሰቡ ጥሩ ሥራ ሠርተው ያለፉ፣ ሥራን ሳይንቁ በዐቅማቸው እየጣሩ መኖር እንደሚቻል የሚያሳዩ ሰዎችን በመምረጥ፣ ታሪካቸውን በገጼ አሠፍራለኹ፡፡” ብሏል።

ኤፍሬም፥ በሳምንት ኣንዴ፣ ለታዋቂ ሰዎች እና ቦታዎች ታሪክ፣ ልዩ ልዩ ርእስ በመስጠት በገጹ ይለጥፋል። “አብ ትሕቲ ጸሓይ አራ”(ከአሥመራ ፀሐይ በታች”) የሚለውን የገጹን ስያሜ ስለ ሰጠበትም ምክንያት፣ ሲያብራራ “ከአንባብያን የተለያዩ ጥያቄዎች ይነሣሉ። “አብ ትሕቲ ጸሓይ አስመራ” የሚለውን ርእስ የተጠቀምኹበት ዋና ምክንያት፣ ኤርትራ ካልኹ ይሰፋብኛል፤ አሥመራ ግን፣ እንደ ኤርትራ ዋና ከተማነቷ፣ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት የሚኖሩባት በመኾኗ፣ ባለታሪኮቹም ልዩ ልዩ ብሔር፣ እምነት እና የኑሮ ደረጃ ያላቸው በመኾናቸው፣ ኹሉንም የኤርትራ ሕዝብ ስለሚወክሉ ነው፡፡” ብሏል።

የፌስቡክ ገጹን በከፈተ ሦስት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ አንድ መቶ የሚደርሱ ታሪኮችን ለአንባብያን እንዳጋራ የሚናገረው ጸሐፊው፣ የገጹ ዓላማ፥ ለባለታሪኮቹ ክብር እና ዕውቅና ለመስጠት በማሰብ እንደኾነ ገልጿል። የተከታዮቹን የተለያዩ አስተያየቶችንም በገጹ እንደሚያስተናግድ የጠቀሰው ኤፍሬም፣ እርምት እና ማስተካከያ የሚያደርግባቸው አስተያየቶችም መኖራቸውን ጠቅሷል።

ገጹ፣ ከተጠበቀው በላይ የብዙዎችን ትኩረት በመሳቡ ገረሜታም ደስታም ፈጥሮለታል። ብዙውን ጊዜ ከተከታዮቹ አዎንታዊ እና አበረታች ኣስተያየቶች እንደሚቀርቡለት ሁሉ፣ አንዳንዴም የማስተካከያ አስተያየቶች እንደሚደርሱት ተናግሯል፡፡ የማስተካከያውን ትክክለኛነት እና አግባብነት አጣርቶ እና ዳግም እርምት አድርጎ በገጹ ላይ እንደሚለጥፋቸው አስረድቷል።

የአንድን ታዋቂ ሰው ወይ ቦታ ታሪክ በማዘጋጀት፣ በፌስቡክ ገጹ ለመለጠፍ ከ500 ናቕፋ በላይ ወጪ እንደሚያደርግ የጠቀሰው ኤፍሬም፣ ከፌስቡክ እንቅስቃሴው ገንዘብ ወይ ትርፍ እንደማይገኝ ጠቅሷል፡፡ የእርሱ ዋና ትርፍ፣ ሰዎችን በጎ በገጹ በማስተዋወቅ፣ ሌሎች ሲማሩበት ማየት እንደኾነ ገልጿል።

በአገሪቱ የኢንተርኔት ትይይዝ ዐቅም ውሱንነት ምክንያት፣ ጹሑፎቹ እና ፎቶዎቹ አነስተኛ መጠን እንዲኖራቸው አድርጎ፣ የትይይዝ ጫናው አንጻራዊ መሻሻል በሚያሳይበት ከንጋቱ 11፡00 ሰዓት እስከ ከጠዋቱ 1፡00 ባለው ጊዜ፣ በግል የኢንተርኔት ካፌዎች በፌስቡክ ገጹ እንደሚጭን አስረድቷል።

“አብ ትሕቲ ጸሓይ ኣስመራ” የሚለው የፌስቡክ ገጹን ለተከታዮች ማጋራት ከጀመረ፣ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ማስቆጠሩን የገለጸው የገጹ ኣዘጋጅ ደራሲ እና ዲሬክተር ኤፍሬም ካህሳይ፣ እስከ አሁን ድረስ፣ የ90 ታዋቂ ሰዎችንና የ10 ቦታዎችን ታሪክ፣ ለተከታዮቹ ማጋራቱን አስታውቋል።

XS
SM
MD
LG