በድጋሚ የታደሰ
ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው ጦርነት “የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን ይበልጥ ሸርሽሮታል” ሲል ለጋዜጠኞች ደኅንነት የሚሟገተው ሲፒጄ ትናንት አስታውቋል።
ሲፒጄ በዚሁ መግለጫው “ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአራት ዓመታት በፊት ወደሥልጣን ሲወጡ መሻሻል አሳይቶ የነበረው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ይዞታ በጥቅምት 2013 ዓ.ም በፌዴራል መንግሥቱና በትግራይ አማፂያን መካከል ጦርነት ከተጫረ ወዲህ አሽቆልቁሏል” ብሏል።
ጦርነቱ ከተቀጣጠለ ወዲህ 63 የሚዲያ ባለሙያዎች መታሠራቸውን ዋና ፅህፈት ቤቱ ዩናይትድ ስቴትስ የሆነው ተሟጋች ቡድን ጠቁሟል።
ካለፈው ዓመት ኅዳር ወዲህ 16 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና ያነሳው ሲፒጄ “ይህም ኢትዮጵያን ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሃራ በስተደቡብ ካሉ ሃገሮች ቀዳሚ ከሆችው ኤርትራ ጋር ያተካክላታል” ብሏል።
አሁን ስምንት ጋዜጠኞች ታስረው እንደሚገኙ ቡድኑ አክሎ አመልክቷል።
“በዚህም - ይላል ሲፒጄ - ኢትዮጵያ ሃሣብን በመግለፅ ነፃነት ሠንጠረዥ ላይ 40 ደረጃ ዝቅ እንድትልና ከ180 ሀገሮች ወደ 140ኛ ደረጃ እንድትወርድ አድርጓታል” ብሏል።
አሁን የፌዴራል መንግሥቱን እየተዋጋ በሚገኘው ህወሓት የበላይነት ይመራ በነበረው የቀደመው መንግሥት የሚዲያ ሥራዎች ላይ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ይካሄድ የነበረ በመሆኑ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ እንዳላት ሲፒጄ አስታውቋል፡፡
የአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደሥልጣን በመጡበት እኤአ 2018 ገደቦችን ለማቅለልና ሀሳብ በነጻነት የሚገለጽበት አዲስ ዘመን ለማምጣት ቃል ገብተው ነበር፡፡
ይሁን እንጂ የመብት ተማጓች ድርጅቶች የትግራዩ ግጭት ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ጋዜጠኞች እስር፣ ዛቻና ጥቃት የደረሰባቸው መሆኑን በመግለጽ የሚዲያ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ዘግበዋል፡፡ ከጥቅምት 2013 ዓም ጀምሮ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች አወዛጋቢ በሆነ ሁኔታ መገደላቸው፣ ለኒው ዮርክ ታይምስና ዘኢኮኖሚስት የሚሰሩት ሁለት ጋዜጠኞች ከአገር እንዲባረሩ መደረጉ ተመልክቷል፡፡ ህወሓት መቀሌን መልሶ ከተቆጣጠረበት ስኔ 2013 ዓም ጀምሮ፣ ያለስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት የምትገኘው ትግራይን ጨምሮ፣ በአገሪቱ በርካታ የመገናኛ ዘዴዎችየተዘጉ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካአገሮች የሲፒጄ ተወካይየሆኑት ሙቶኪ ሙሞየታሰሩት ጋዜጠኞች “ስለጦርነቱ ከዋናው የመንግሥት ትረካ የተለየ” ዘገባዎችን የሠሩ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
“አንዳንዶቹ ጋዜጠኞች ሥራቸው የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖችን ሊጠቅም ይችላል ተብሎ ስለታሰበ ኢላማ ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ውስጥ ግን፣ እኛ ልንናገር የምንችለው እነዚህ እስሮች የሚያሳዩት የጋዜጠኝነትና የትችት ሥራ ከወንጀል ድርጊቶች ጋር እየተምታታ መሆኑንነው፣ ያ ደግሞ በጣም አደገኛ ነው፡፡” ብለዋል ሙቶኪ፡፡
ለጋዜጠኞች ደኅንነት የሚሟገተው ሲፒጄ የመዘገባቸው ቢያንስ 8 ጋዜጠኞችና የሚዲያ ሠራተኞች አሁን በእስር ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡
አብዛኞቹ እስሮች የሚፈጸሙበት መንገድ “ተመሳሳይነት” ያላቸው መሆኑን የገለጸውሲፒጄ፣ ጋዜጠኞቹ ምንም ክስ ሳይመሰርታበቸው፣ ባለሥልጣናት ረጅም የምርመራ ጊዜ እየጠየቁባቸው፣ ለበርካታ ሳምንታት እንደሚቆዩ አመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ጋዜጠኞችን ኢላማ እንደማያደርግ፣ ፖሊሲ ተገቢውን አሰራርና ሂደቱን ተከትሎ እንደሚሠራና የሚታሰሩትም የአገሪቱን የሚዲያ ህግ የጣሱትን ብቻ እንደሆኑ ገልጾቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ የቀረበበትን ክስ አስተባብሏል፡፡