በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሽብር ክስ በጋዜጠኞች ላይ ተመሠረተ


የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብር ሤራ ተሣትፈዋል ባላቸው በአንድ የጋዜጣ ምክትል አዘጋጅና ሌላ አምደኛ ላይ በይፋ ክስ መመሥረቱን ሲፒጄ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሽብር ሤራ ተሳትፈዋል ያላቸውን ሁለት ጋዜጠኞች ማሠሩን ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን (ሲፒጄ) አስታወቀ። እርምጃው መታየት ያለበት መንግሥት ትችት የሚያቀርቡበትን የነፃውን ፕሬስ ጋዜጠኞች ለማፈንና ለማሠር የተጋነኑ ክሦችን እየተጠቀመ ካለበት የቆየ አሠራሩ ጋር ነው ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይ ግን የጋዜጠኞቹ መታሠር ፈጽሞ ከጻፉት ነገር ጋር በተያያዘ አይደለም ብለዋል፡፡

ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት የአውራምባ ታይምስ ምክትል ዋና አዘጋጅ ውብሸት ታዬና የሣምንታዊው የፍትሕ ጋዜጣ ባለ አምድ ርዕዮት ዓለሙ ካለፈው ሣምንት ጀምሮ መታሠራቸውን ሪፖርት ያደረገውም የተለያዩ የዜና ዘገባዎችና የአገር ውስጥ ጋዜጠኞችን መሠረት በማድረግ መሆኑን ገልጿል።

መንግሥት የታገደውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ግንቦት ሰባትን ጨምሮ «አሸባሪ» ሲል የሰየማቸውን ቡድኖች ይደግፋሉ ብሎ ያመነባቸውን ጽሑፎች በሚያቀርቡ ላይ የኢትዮጵያ ፀረ-ሽብር ሕግ ተግባራዊ ይሆናል።

ሕጉ በጋዜጠኞች ላይ ተግባራዊ የሆነውም ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ በሲፒጄ ሪፖርት ላይ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ደግሞ የጠረጠራቸውን ዘጠኝ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቋል።

ፖሊስ “የውጭ ኃይሎች መሣሪያ በመሆን በሽብር ሥራ ላይ ተሠማርው ሲንቀሳቀሱ ነበሩ” ያላቸውን ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወቀው ረቡዕ ሰኔ 22 / 2003 ዓ.ም ነው።

ግለሰቦቹ የተያዙት ከአገር ውስጥ ፀረ-ሰላም ኃይሎችና ከሻዕቢያ ጋር በማበር በኤሌክትሪክ ማሠራጫዎችና በስልክ መስመሮች ላይ ጉዳት በማድረስ አገሪቱን ወደ ሽብርና ሁከት ቀጠናነት ለመቀየር ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው እንደሆነም ተገልጿል።

በአሸባሪነት የወንጀል ተግባር ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ዘጠኝ ግለሰቦች መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ዘርይሁን ገብረእግዚብሔር፣ እና የዚሁ ፓርቲ አባል አቶ ደጀኔ ተፈራ ይገኙበታል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው ምርመራ ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተነግሯል።

ከሌሎቹ ሰባት ሰዎች ጋር መሆኑ ነው ውብሸት ታዬ የአውራአምባ ታይምስ ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅና በመምህርነት ሙያ የተሠማሩት ወይዘሪት ርዕዮት ዓለሙ ተይዘው የታሠሩት።

ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና ባለ አምዷ ርዕዮት ዓለሙ በሽብር ተግባር ተጠርጥረው መታሠራቸው አሳሳቢ መሆኑን ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች ደኅንነት ተሟጋች ቡድን - ሲፒጄ ገልፆ ባስቸኳይ እንዲፈቱ ጥሪ አስተላልፏል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል በበኩላቸው ጋዜጠኛውና ባለአምዷ የታሠሩት ፈጽሞ ከፃፉት ነገር ጋር በተያያዘ እንዳልሆነ ለብሉምበርግ ኒውስ መግለጻቸው ተዘግቧል። ሲፒጄ እንደሚለው ግን ርዕዮት በቅርቡ ባቀረቡት ፅሁፋቸው ገዢው ፓርቲ ለሚሌንየም ግድብ ፕሮዤ ከሕዝብ የገንዘብ መዋጮ አሰባሰቡን ዘዴ መተቸታቸውን፥ ጋዜጠኛ ውብሸት ደግሞ ስለአካባቢው ፖለቲካ ሁኔታ መጻፉን ገልጿል።

ከታሠሩ ከሰኔ 14 ቀን 2003 ዓ ም ጀምሮ፥ የሕግ ባለሞያ እንዲያያቸው መንግሥት ተደጋጋሚ ጥያቄ ቀርቦለት የከለከለ መሆኑን፥ እናታቸው ግን ዛሬ (ሐሙስ) ላጭር ጊዜ ገብተው እንዲጐበኟቸው ተፈቅዶላቸው እንደነበር የርዕዮት ወላጅ አባት አቶ ዓለሙ ጎቤቦ ተናግረዋል።

ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት - አምነስቲ ኢንተርናሽናል ደግሞ፥ የጋዜጠኞቹንና የተቃዋሚ ፓርቲዎቹን አባላት መታሠር በመቃወም የበኩሉን መግለጫ አውጥቷል።

«በተለይ መንግሥቱን የሚተቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የነፃውን ፕሬስ አባላት ለማፈን ፀረ-ሽብር ሕጉን መጠቀሚያ ማድረግ አሳሳቢ ነው» ብሏል።

አገር ውስጥ በሕጋዊነት ተቋቁመው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት እየታፈሱ የሚታሠሩትም ይህንኑ ሕግ በመጠቀም ነው ብሏል።

ታሣሪዎቹን የሕግ አማካሪዎች ወይም ጠበቆችና ቤተሰቦቻቸው እንዲጐበኟቸውም ፈቃድ ማግኘት እንዳለባቸው አስገንዝቧል አምነስቲ።

ክሌር ቤስተን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ጉዳይ አጥኚ ናቸው፤ እንዲህ ይላሉ፡- “ፀረ-ሽብር ሕጉ ግልፅ አለመሆኑ አምነስቲን ሲያሳስብ ቆይቷል። ምክንያቱም ህጉ በነፃ የመሰብሰብና የመናገር መብትን ይገድባል። ለምሳሌ በአሸባሪነት የተሰየሙ ድርጅቶችን ወይንም ሰዎችን ስም በፅሁፋቸው መጥቀስም በአሸባሪነት ያስከስሳል ያሳስራል።”

አንዳንዶቹ ታሣሪዎች ለስቃይ አያያዝ ሊጋለጡ ይችላሉ ሲልም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዚሁ መግለጫው አሳስቧል።

በሌላ በኩል ፀረ-ሽብር ሕጉ ሙያቸውን በሕጋዊ መንገድ ለሚያራምዱ ጋዜጠኞች ስጋት እንዳልሆነ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት መግለፁን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰኔ 22 / 2003 ዓ.ም ዘግቧል።

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG