የባይደን አስተዳደር አዲስ የተከሰተውን የኦሚኮርን የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ ለመቋቋም ሲባል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሚመጡ መንገደኞች ላይ ጥብቅ መስፈርትና መመሪያ ለማውጣት እየተዘጋጀ መሆኑን ተሰማ፡፡
ዘገባዎች እንዳመለከቱት መመሪያው መንገደኞች ተከተቡም አልተከተቡም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከሚጓዙበት አንድ ቀን ቀደም ብለው የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረግ ያለባቸው መሆኑን እንደሚያካትት ተነግሯል፡፡
ባለሥልጣናቱ መንገደኞች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ከገቡ በኋላ ለሰባት ቀናት ራሳቸውን አግልለው እንዲቆዩና እንዲሁም በገቡ ከሦስት እስከ አምስት ቀናት ውስጥ እንደገና ምርመራ እንዲያደርጉ ለመወሰን እየተነጋገሩ መሆኑን ተዘግቧል፡፡
መመሪያው ተፈጻሚ የሚሆነው ከውጭ በሚመለሱ በሁሉም የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎች ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደን የአስተዳደራቸውን አዲስ ስትራቴጂ ነገ ሀሙስ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 ልዩ ዝርያ የኦሚኮርን ቫይረስ ታይቷል ከተባለበት ቀን አንስቶ ከውጭ ወደ አገራቸው በሚገቡ መንገደኞች ላይ የጉዞ ማዕቀብ ከጣሉ በርካታ ሃገሮች ጋር እየተቀላቀለች መሆኑም ተዘግቧል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ግን፣ የጎዞ ማዕቀቡ ኮቪድ-19 አስመልክቶ አገሮች ያላቸውን አዳዲስ መረጃ እንዳያጋሩ ስለሚያደርግ ወረርሽኙን ለመቋቋም ያለውን አለም አቀፍ ጥረት ይጎዳል ሲል አስጠንቅቋል፡፡