ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጤና ጥበቃ ሥርዓታቸውን ያጠናከሩት ሀገሮች፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት፣ የተሻለ ውጤት ማሳየታቸውን፣ የዓለም የጤና ድርጅት ትናንት ገልጿል።
የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ቴድሮስ አድሐኖም፤ ትላንት ባደረጉት ዕለታዊ መግለጫ፣ ሃገሮች ለቀጣዩ ለመዘጋጀት እንዲችሉ፣ ከወቅቱ የወረርሽኝ ሁኔታ መማር ይኖርባቸዋል ብለዋል። ታይላንድን፣ ሞንጎልያን፣ ሴነጋልንና ሌሎች ሀገሮችን፣ ዓለምቀፉን ወረርሽኝ ለመከላከል ላደረጉት ጥረት አሞግሰዋቸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ስፔን ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎች ብዛት፣ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ለመድረስ፣ የመጀመሪያዋ የአውሮፓ ሃገር ሆናለች። በዓለም ደረጃ 27.3 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች፣ በኮቪድ-19 መያዛቸው ታውቋል። በሞት የተለዩት ደግሞ 893,000 ደርሰዋል።
ከስፔን የጤና ሚኒስቴር በተገኘው አሃዝ መሰረት፣ እስከዛሬ ባለው ጊዜ 525,549 የቫይረሱ በሽተኞች አሏት። የሞቱት 29,516 መድረሳቸው ተገልጿል። ፈረንሳይ ውስጥ 367,174 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ፣ በሞት የተለዩት 30,732 መሆናቸውን፣ በብሪታንያ ደግሞ 352,451 የኮቪድ 19 በሽተኞ መኖራቸውን፣ የሞቱት 41,643 መሆናቸውን፣ የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል።
ደቡብ ኮርያ ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የህክምና ሰልጣኞች፣ ለሦስት ሳምንታት ለሚጠጋ ጊዜ ሥራ ካቆሙ በኋላ፣ ዛሬ ወደ ሥራ ገበታቸው ተመልሰዋል። የነሱ ሥራ ማቆም በአዲስ መልክ ያገረሽውን፣ የኮቪድ-19 መዛመትን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዳወሳሰበ ተገልጿል።
የህክምና ስልጣኞቹ እአአ ነሃሴ 21 ቀን ሥራ ያቆሙት፣ መንግሥት በህክምና ትምህርት ቤቶች ላይ የደርገውን ለውጥ በመቃወም ነው። እነዚህ ሥራ አቁመው የነበሩት ሰልጣኖች፣ በአስቸኳይ የህክምና ክፍሎችና በጠና የታመሙ ሰዎች በሚታከሙባቸው ክፍሎች፣ ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ ትልልቅ ሆስፒታሎችን ጎድቶ መቆየቱ ታውቋል።