ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፖብሊክ ውስጥ የፊታችን ዕሁድ ይካሄዳል ከተባለው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጭ እንዲሆኑ መወሰኑ ያስቆጣቸው የሃገሪቱ ምሥራቃዊ አካባቢዎች ነዋሪዎች ያደረጉትን ሰልፍ ለመበተን ፖሊስ ዛሬ በወሰደው ዕርምጃ በተቃዋሚዎች ላይ ቀጥተኛ ተኩስ መክፈቱና አስለቃሽ ጋዝ መርጨቱ ተዘግቧል።
ቤኒ በምትባለው ከተማ እንዲሁም ቡቴምቦና በአካባቢዎቻቸውም ባለው የገዳዩ ኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት ድምፅ መስጠቱን ወደ ፊታችን መጋቢት ማዘዋወሩን የምርጫ ኮሚሽኑ ካሣወቀ በኋላ በአሥሮች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በቤኒ ከተማ ጎዳናዎች ላይ ጎማ እያቃጠሉ ቁጣቸውን ከመግለፃቸውም በላይ በኢቦላ ሕክምናና እንክብካቤ ማዕከላት ላይም ጥቃት ማድረሳቸው ታውቋል።
ቤኒ ከተማ ውስጥ ወደ ምርጫ ኮሚሽን ፅሕፈት ቤት የሄዱ ተቃዋሚዎች በዕሁዱ ምርጫ ላይ ከመላ ሃገሪቱ ጋር ድምፅ የመስጠት መብታቸው እንዲከበርላቸውና የምርጫ ኮሚሽኑ ፕሬዚዳንትም ከሥራቸው እንዲነሡ ጠይቀዋል።
የምርጫ ኮሚሽኑ በተጨማሪም በምዕራብ ኮንጎም በሚስተዋለው የጎሣ ግጭት ምክንያት ድምፅ መስጠቱ በዩምቢ ከተማም እንዲተላለፍ ወስኗል።
ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፖብሊክ የአሁኑን ምርጫ የምታካሄደው ከእርሣቸው የቀደሙት ፕሬዚዳንት አባታቸው ሎረን ዴዚሬ ካቢላ የዛሬ 17 ዓመት እንደተገደሉ መንበረ ሥልጣኑን ይዘው የቆዩትን ጆዜፍ ካቢላን ለመተካት ነው።
ምርጫው ይካሄዳል የተባለው ከሁለት ዓመታት በፊት የነበረ ቢሆንም በየወቅቱ እየተላለፈ መቆየቱ በሃገሪቱ ውስጥ ብዙ ሁከቶችና አመፆችን ሲያስከትል ቆይቷል።
ዕርምጃዎቹ ካቢላ የሚፈልጓቸውን ዕጩ ኢማኑኤል ራማዛኒ ሻዳሪን ለማገዝ የሚወሰዱ ናቸው ሲሉ የአካባቢው ፖለቲከኞች ወቀሣ ያሰማሉ።
የኮንጎ ግዙፉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፌሊክስ ቺሴኬዲ የቀድሞ እንደራሴ የሆኑት የአሁን የሞቢል ኤክሰን ሥራ አስኪያጅ ማርቲን ፋዩሉ ከሃያ አንድ የሻዳሪን ተቀናቃኞች መካከል ናቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ