በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ እጅግ አሠቃቂ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ


በትግራይ ያለው ሰብአዊ ቀውስ እጅግ አሠቃቂ ደረጃ ላይ መድረሱ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:36 0:00

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊ ቀውስ፣ እጅግ አሠቃቂ ደረጃ ላይ በመድረሱ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ትኩረት እንደሚሻ አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ በአወጣው መግለጫ፣ የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ/USAID/ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም/WFP/ ለትግራይ ክልል ሲያቀርቡት የነበረውን ሰብአዊ ርዳታ በማቋረጣቸው፣ ተረጅዎች ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዲሬክተር አቶ ኄኖክ መለሰ፣ ስለ መግለጫው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣ ርምጃው ተረጅዎችን ለከፋ ችግር እያጋለጠ በመኾኑ፣ ድርጅቶቹ ያቋረጡትን የርዳታ አቅርቦት መልሰው እንዲያስጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አርብ ግንቦት 11 ቀን 2015 ዓ.ም ያወጣውን መግለጫ በተመለከተ ለአሜሪካ ድምፅ ማብራሪያ የሰጡት የምክር ቤቱ ዋና ዲሬክተር አቶ ኄኖክ መለሰ፣ ሁለቱም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የርዳታ አቅርቦቱን ለማቋረጥ ከወሰኑ በኋላ፣ የም/ቤቱ አባላት በትግራይ ክልል ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በጉብኝታቸው ወቅት፣ ሰብአዊ ቀውሱ ከባድ መኾኑን ተመልክተናል፤ ያሉት ዋና ዲሬክተሩ፣ርዳታውን ማቋረጥ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለችግር ስለሚያጋልጥ፣ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶቹ፣ ውሳኔያቸውን መልሰው እንዲያጤኑት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት፣ በትግራይ የተቋረጠውን ርዳታ መልሶ ለማስጀመር የሚደረግን ማንኛውንም ጥረት ለመደገፍ ዝግጁ መኾኑን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ/USAID/ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም/WFP/፣ በትግራይ ክልል ሲያከናውኑት የቆዩትን የምግብ ርዳታ ሥርጭት፣ በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን ያስታወቁት ከ20 ቀናት በፊት ነበር፡፡ ለጋሽ ድርጅቶቹ፣ ከውሳኔው ላይ የደረሱት፣ ለሰብአዊ ርዳታ የገባው እህል፣ ከዓላማው ውጪ እየተመዘበረ ለገበያ በመቅረቡ እንደኾነ በወቅቱ አመልክተዋል፡፡

አቶ ኄኖክ መለሰ፣ የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶቹን ውሳኔ ባይቀበሉትም፣ ለችግረኛ ተረጂዎች የሚቀርበውን ሰብአዊ ርዳታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ ለገበያ ማቅረብ ግን ትክክል እና ተገቢ አለመኾኑን አስረድተዋል፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በዓለም አቀፍ ለጋሾች የቀረበው ርዳታ ለገበያ ስለመዋሉ የሚያጣራ ግብረ ኃይል ማቋቋሙን አስታውቋል። ሰብአዊ ርዳታ እንዲከፋፈል ማመቻቸት እንጂ፣ የርዳታ እህል ማከፋፈል ሥራው አለመኾኑን የገለጸው የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ፣ በድርጊቱ ላይ የሚደረገውን ምርመራ እንደሚደግፍ ገልጿል፡፡

XS
SM
MD
LG