በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቻድ ጄኔራል ዴቢ በምርጫው ካሸነፉ በኋላ ወታደሮችዋን አሰማራች


ፎቶ ፋይል፡ የሽግግር ፕሬዚዳንት የሆኑት ጄኔራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በበንጃሜና
ፎቶ ፋይል፡ የሽግግር ፕሬዚዳንት የሆኑት ጄኔራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በበንጃሜና

በምዕራብ አፍሪካዊቷ ቻድ እኤአ ግንቦት 6 የተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ትላንት ሐሙስ ምሽት ይፋ ከተደረገ በኋላ ቻድ ሰላሟን ለማስጠበቅ ወታደሮቿን አሰማርታለች፡፡

ወታደሮቹ በሀገሪቱ ዋና ከተማ በንጃሜና የተሰማሩት የሽግግር ፕሬዚዳንት የሆኑት ጄኔራል ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 61 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ መሆናቸውን መገለጹን ተከትሎ ነው፡፡

ዋናው የተቃዋሚ ፓርቲ እጩ ሰክሴ ማስራ “በምርጫው ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት አሸንፈናል” በማለት የምርጫው ውጤት ተሰርቆብኛል ብለዋል።

ከንጃሜና ነዋሪዎች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ትላንት ምሽት ውጤቱ ከተገለጸ በኋላ ዛሬ ዓርብ ማለዳው ላይ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ተሰምቷል፡፡

የመንግሥት ቴሌቪዥን የተኩስ ድምጾች መሰማታቸውን ቢገልጽም የተኩሱ ባለቤት ማን እንደሆነ ለይቶ አላመለከተም፡፡

የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የተኩስ ድምጽ የምርጫውን ውጤት የሚቃወሙትን ለማስፈራራት በመንግሥት ኃይሎች የተተኮሰ ሳይሆን እንዳልቀረ ገምተዋል፡፡

ተቃዋሚዎች እና የሲቪል ማኅበራት በአወዛጋቢው የምርጫ ውጤት ምክንያት ሁከት ሊፈጠር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡

በመላ ቻድ በተለይም በመዲናዋ ሊፍጠር ይችላል የተባለውን ግጭት ከወዲሁ ለመከላከል መንግሥት የምርጫው ውጤት ከመገለጹ አስቀድሞ የፖሊስ ኃይል ማሰማራቱ ተናግሯል፡፡

ፕሬዚዳንት ዴቢ ምሽቱን በሰጡት መግለጫ አብዛኛው መራጮች እሳቸውን በመምረጣቸው አመሰግነው ካሁን በኋላ “ ለሁሉም የቻድ ዜጎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ ፕሬዚዳንት” መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ብሄራዊ የምርጫ ኮሚሽን ለመምረጥ ከተመዘገቡት 75 ከመቶ መራጮች መካከል 8.2 ሚሊዮን የሚሆኑት በምርጫው መሳተፋቸውን ገልጿል፡፡ የዴቢ ዋነኛው ተፎካካፊ ሰክሴ ማስራ 18 ከመቶ ማግኘታቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል፡፡

ዴቢ ወደ ስልጣን የመጡት እኤአ 2021 ቻድን ለ30 ዓመታት የመሩት አባታቸው ኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ከሞቱ በኋላ ነው፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG