የዩናይትድ ስቴትስ የጤና ባለሥልጣናት ለኮሮናቫይረስ የተጋለጡ ሰዎች በመገለል የሚቆዩበትን ጊዜ ከአስር ቀን ወደ አምስት ቀን ማጠሩን አስታወቁ፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል ሲዲሲ ባለሥልጣናት ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎች ራሳቸውን አግልለው ከቆዩበት አምስት ቀን በኋላ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን በማድረግ ወደ ህብረተሰቡ ተመልሰው መቀላቀል የሚችሉ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የሲዲሲ ባለሥልጣናት ቫይረሱ የበለጠ ተላላፊ የሚሆነው ምልክቱ ከታየበት ሁለት ቀናት በፊትና ምልክቱ ከሄደበት ሶስት ቀናት በኋላ ድረስ መሆኑን በልምድ መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ ምክረ ሀሳቡ አስገዳጅ መመሪያ ሳይሆን ለአሠሪዎች፣ ለክፍለ ግዛትና፣ የየአካባቢው ባለሥልጣናት ጠቃሚ መመሪያ እንዲሆን ታስቦ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ይሁን እንጂ ውሳኔው የመጣው ጎጀኒነቱ እንደከዚህ በፊቶቹ ቫይረሶች ባይሆንም የሚስፋፋበት ጊዜ እጅግ ፈጣን መሆኑ ከተነገረው የኦምሪኮን ቫይረስ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ቫይረሱ ብዙ ሰዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚይዝ በመሆኑ ሀኪሞችን ጨምሮ በመገለል እንዲቆዩ የሚደረጉ ሰዎች ሊበዙ እንደሚችሉ ተሰግቷል፡፡
ያ ከሆነ ደግሞ እንደ ሆስፒታል የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎት ሰጭዎች በሀኪሞች እጥረትና በህሙማን ብዛት ሊጨናንቀቁ ስለሚችል መመሪያው የወጣው ቀውስ እንዳያመጣ ከመነጨ ሥጋት ጭምር መሆኑም በዘገባው ተመልክቷል፡፡