ትላንት ረቡዕ የዩናይትድ ስቴትስ ሰሜን ምዕራባዊ ግዛትን የመታው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በፈጠረው ከባድ ዝናብና ነፋስ፣ ቢያንስ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ።
ትላንት ረቡዕ በዋሽንግተን ክፍለ ግዛት በደረሰው ከባድ የአውሎ ነፋስ አደጋ በዋሽንግተን ግዛት በየ460 ሺሕ ቤቶች የመብራት ኃይል መቆራረጥ አስከትሏል፡፡
ዛፎች በየቦታው መውደቃቸውም ታውቋል። በፍጥነት ኃይሉ እየጨመረ ይኼዳል የተባለው ይኸው ከባድ አውሎ ንፋስ ቦምብ ሳይክሎን (Bomb cyclone) በሚል ስያሜ ይታወቃል፡፡
በኦሬገን፣ ካሊፎርኒያ እና ኔቫዳም የኃይል መቋረጥ ተከስቷል፡፡ በዚህ ሳቢያ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ የነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ተስተጓጉሏል። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ አካባቢውን መምታት የጀመረው አውሎ ነፋስ፣ ኃይሉ እየጨመረና እየጠነከረ እንደሚሄድ ተነግሯል፡፡
የአየር ሁኔታ ትንበያ ማእከል፣ በካሊፎኒያ ሰሜን ሳን ፍራንሲስኮ አካባቢ፣ እስከ ነገ አርብ ድረስ ከመጠን በላይ ዝናብ እንደሚጥል ገልጾ፣ የጎርፍ አደጋ ማስጠንቀቂያዎችን እስከ ቅዳሜ አራዝሟል፡፡
መድረክ / ፎረም