በአሜሪካ በሚቀጥለው ሳምንት በሚደረገው የፕሬዚዳንታዊ አጋማሽ ግዜ ምርጫ 80 ሚሊዮን የሚሆኑ ድምጽ ሰጪዎች ከእንግሊዘኛ ውጪ ባሉ ቋንቋዎች ድምጽ የመስጠት አማራጭ ይኖራቸዋል ተብሏል።
ይህም የፌዴራል መንግሥቱ አንዳንድ የማኅበርሰብ ክፍሎች በቋንቋቸው እንዲገለገሉ በማሰብ ያወጣውን ደንብ መሠረት በማድረግ መሆኑ ታውቋል።
“ሃሳቡ በታሪክ ከምርጫ ሂደት የተገለሉ ማኅበረሰቦችን እንዲሳተፉ ለማድረግና፣ ለምርጫው ባይተዋር እንዳይሆኑ ለማድረግ ነው” ብለዋል ቦይዚ ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የሚገኘው የአይዳሆ ፖሊሲ ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ጌብ ኦስተርሃውት።
በእአአ 1965 መጀመሪያ የወጣው ድምጽ የመስጠት መብት በሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍል ያሉ ጥቁር አሜሪካውያን ላይ ያተኮረ የነበረ ሲሆን ደንቡ በ1975 ሲስፋፋ ሌሎች ህዳጣን ማኅበረሰቦችንም እንዲያካትት ሆኗል።
ይህም ነባሮቹ አሜሪካውያንተወላጆች (ኔቲቭ አሜሪካን) የሚባሉትን፣ እንዲሁም የአላስካ፣ ላቲኖስ ወይም ከደቡብ አሜሪካ የመጡ ማኅበረሰቦችን እና የእሲያ አሜሪካውያንን እንዲያካትት ሆኗል።
“በእንግሊዝኛ የሚዘጋጁት የድምጽ ወረቀቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለተማሩ ሰዎች ወይም ሌላ ቋንቋ ለማይናገሩ ሰዎች ፈተና በመሆኑ አግላይ ነው። በምርጫ እንዳይሳተፉ እንቅፋት ይሆናል” ይላሉ የምርጫ መብት ፕሮጀክት የተሰኘው ተቋም አማካሪ የሆኑት ጂም ተከር።
የአሜሪካ የሕዝብ ቆጠራ ቢሮ በየአምስት ዓመቱ የትኞቹ እዳጣን ማኅበረሰቦች በቋንቋቸው መስተናገድ እንዳለባቸው ይወስናል። ይህም በአንድ አካባቢ ከ5በመቶ በላይ የሚሆኑ መራጮች የእንግሊኛ ቋንቋ ችሎታቸው ውስን ክሆነ፣ ወይም በአንድ የምርጫ ክልል ከ10ሺ በላይ መራጮች እንግሊዝኛን በሚገባ የማይናገሩ ከሆነ በምርጫ ወቅት በቋንቋቸው በሚዘጋጅ ሰነድ ይስተናገዳሉ።
የአካባቢ የምርጫ ባለሥልጣናትም የድምጽ ቁሳቁሶችንም ሆነ የድምጽ ሳጥኖችን በተመረጡት የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች እንዲያዘጋጁ ይጠበቅባቸዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የከተማው አስተዳደር አማርኛን ከእንግሊዝኛ እንደ አንድ ሥራ ቋንቋ ስለሚቆጥረው፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለማንኛውም የመንግሥት መ/ቤቶች ጉዳይ በዚሁ ቋንቋ ይገለገላሉ። በምርጫ ወቅትም እንዲሁ። ትውልደ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚገኙባቸው ሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች በደንቡ መሠረት በምርጫው ወቅት በአፍ መፍቻ የቋንቋቸው ተገልጋይ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።