ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሚቀጥለው ወር ጀኔቭ ላይ በሚደረገው ስብሰባ ከራሽያው ፕሬዚዳት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ዋይት ሀውስ ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ ይህ የሚሆነው የባይደን አስተዳደር በሁለቱ አገሮች መካከለው የሻከረውን ግንኑነት ወደነበረበት ለመለስ ጥረት በማድረግ ላይ በሚገኝበት ባሁኑ ወቅት ነው፡፡ አንዳንድ የሪፐብሊካን ህግ አውጭዎች፣ የሞስኮ ወዳጅ ቤላሩስ እየያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ አስመልከቶ ያሳሰባቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የባይደንን አስተዳደር ውሳኔ ተቃውመዋል፡፡
በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን እና በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ እኤአ ሰኔ 16፣ በጄኔቫ የሚካሄደው፣ የዩናይትድ ስቴትስና የራሽያ ጉባኤ፣ በብራስልስ የሚደረገውን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ወይም የኔቶ አባል አገራት ጉባኤን ተከትሎ፣ የሚከናወን መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሁለቱ መሪዎች፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን፣ የአየር ንብረት ለውጥን፣ እንደገና ስለሚታደሰው የኢራን የኒኩልየር ስምምንት ጨምሮ፣ በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንደሚነጋገሩ ተመልክቷል፡፡
ዋይት ሀውስ እንዳረጋገጠው፣ የራሽያ አጋር በሆነችው ቤላሩስ ሰሞኑን የተፈጸመው ነገር ቢኖርምባይደን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ይገናኛሉ፡፡
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ ስለዚሁ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል
“ፕሬዚዳንቱ የቤላሩስን ጉዳይ በእጅጉ ያሳሰባቸው መሆኑን በውውይታቸው ወቅት ለማንሳት እቅዱ አላቸው፡፡”
ባለፈው እሁድ የፑቲን ወዳጅ የሆኑት የቤላሩስ ፕሬዘዳንት አሌክዛንደር ሉካሼንኮ የሳቸው መንግሥትን ይተቻል የተባለውን ጋዜጠኛ ራማን ፕራታስቪች ያጓጉዝ የነበረውን የትንራስፖርት አውሮፕላን አቅጣጫውን እንዲቀየር ማድረጋቸው ተነግሯል፡፡
የ”ኢሮሽያ ሴንተር ኢን ዘ አትላንቲክ ካውንስል” የተባለው ተቋም ዳይሬክተር ጆን ኸርብስት እንዲህ ይላሉ
“ሉካሼንኮ ያደርጉት ነገር እጅግ የሚስያቆጣ ነው፡፡ በአየር ትራንስፖርት ላይ የተፈጸመ ውንብድና ወይም የአየር ላይ ሽብርተኝነት ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ተግባር ቅጣት መኖር አለበት፡፡ የአሮውፓ ህብረት ያለምንም ማመንታት ፈጥኖ እርምጃ እንደሚወስድ አምናለሁ፡፡ የቤላሩስ አየር መንገድም ሆነ ወደ ቤላቪያ ለሚደረግ በረራ፣ የአውሮፓ ህብረትን አውሮፕላን ማረፊያዎች ወይም የአየር ክልል እንዳይጠቀሙ ስለ ማገድ መነጋገር ይቻላል፡፡”
ሞስኮ በጉዳዩ ጣልቃ እንዳልገባች አስተባብላለች፡፡ ባይደን ድርጊቱን አውገዘው የቤላሩሲያን ህዝብ ለዲሞክራሲ የሚያደርገውን ትግል እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡
ሉካሼንኮ ለ27 ዓመታት በሥልጣን የቆዩ መሪ ናቸው፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ የሪፐብሊካን አባላት ውሳኔው በቂ አይደለም ይላሉ፡፡
ሪፐብሊካኑ ሴንተር ቤን ሳስ፣ ጉዳዩን አስመልከቶ ባወጡት መግለጫ፣ “ባይደን ፑቲንን እንደ ጉልበተኛ (ጋንግስተር) ከማየት ይልቅ፣ በዚህ ጉባኤ በመሳተፍ፣ ከራሽያ ጀርመን ድረስ ጥንድ ሆኖ የተዘረጋውን የኖርድ ስትሪም 2ን የጋዝ ማስተላለፊያ መስመርን አጎናጽፈው በድርጊታቸው እንዲበረቱ እያደረጓቸው ነው” ብለዋል፡፡
የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ አሁንም እንዲህ ይላሉ
“ከራሽያ ፕሬዚዳንት ጋር የምናደርገውን ውይይት እንደ ሽልማት አንቆጥረውም፡፡ የአሜሪካን መሰረታዊ ጥቅም የመከላከል አንዱ አካል አድርገን ነው የምንወስደው፡፡ ፕሬዚዳንት ባይደን ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር የሚገናኙት በአገሮቻችን መካከል ልዩነት ስላለ ነው፣ እንጂ በልዩነቶቹ ምክንያትን አይደለም፡፡”
ዩናይትድ ስቴትስ ከራሽያ አንስቶ፣ እስከ ጀመርን የተዘረጋውን የኖርድ ስትሪም 2 የጋዝ ማስተላለፊያን ለማገድ፣ ለረጅም ዐመታት ሠርታለች፡፡ የባይደን አስተዳደርም በመጠናቀቅ ላይ ባለው የማስተላለፊያው ፕሮጀክት በተሳተፉት የራሽያ ድርጅቶች ላይ ሁሉ ማእቀብ ጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ በጀርመን በኩል ፕሮጀክቱን በበላይነት በመቆጣጠር የተሳተፉ የጀርመን ኩባንያዎች ከማዕቀቡ ነጻ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ ያም የተደረገው ከአትላንቲክ ባሻገር ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆን በመታሰቡ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
በአውሮፓ በሚገኘው የካርኒጌ ኢውሮፕ የስትራቴጂክ ብሎግ ዋና አዘጋጅ የሆኑት ጁዲ ዴምፕሲ እንዲህ ብለዋል
“የባይደን አስተዳደር አውሮፓውያኑን በተለይም ጀርመንን ወደራሳቸው መሳብ ይኖርባቸዋል፡፡ የራሽያ ስትራቴጄ ሁሌም ከአትላንቲክ ባሻገር ያለውን ግንኙነት ማዳካም ነው፣ የምዕራቡን አለምና አውሮፓን መከፋፈል ነው፡፡ ስለዚህ የአውሮፓ አገሮች በመተባበር የባይደንን ጥረት መደገፍ ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው፡፡”
ዋይት ሀውስ በመግለጫው ፣ ባይደን ሞስኮ በዩክሬን ላይ ያላትን ጠብ አጫሪነት በውይይታቸው እንደሚያነሱ ጠቅሶ ፣ ይሁን እንጂ አስተዳደሩ በዩናይትድ ስቴትስ እና ራሽያ መካከል ያለው ግንኙነት አቅጣጫው የሚታወቅና የተረጋጋ እንዲሆን በማድረጉ ላይ እንደሚያተኩር አስታውቋል፡፡
የዋይት ሀውስ ሪፖርተር ፓትሲ ውዳክስዋራ ካጠናቀረችው ዘገባ የተወሰደ፡፡