በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ 500 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ለገሰች


ዩናይትድ ስቴትስ 500 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ለገሰች
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:58 0:00

ዩናይትድ ስቴትስ 500 ሚሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ለገሰች

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ትናንት ረቡዕ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን በድረ ገጽ የኮቪድ 19 ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ ዓላማው እኤአ በ2022 የኮቪድ 19 ቫይረስን ድል ለመንሳት፣ የዓለም መሪዎችን የበጎ አድራጊዎችን፣ የሲቪል ማህበረሰብ አባላትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ኢንዱስትሪዎችን ለማስተባበር ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተጨማሪም ግማሽ ቢሊዮን፣ የፋይዘር ክትባት መድሃኒቶችን ልገሳ ይፋ አድርገዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ከዓለም መሪዎች ጋር በድረ ገጽ ባካሄዱት ስብሰባቸው

“ወረርሽኙን እንዲያበቃ ለመታገል እንደገና ቃል እንግባ” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ፕሬዚዳንት 500 ሚሊዮን ተጨማሪ የፋይዘር ክትባት መድሃኒቶችን በመለገስ የዩናይትድ ስቴትስን ጠቅላላ ድርሻ ወደ 1.1 ቢሊዮን ለማሳደግ ቃል እንዲህ በማለት ገብተዋል፡፡

“በአሜሪካ እስከዛሬ ለእያንዳንዱ ሰው እንዳደረግነው አሁን ደግሞ ለተቀረው ዓለም ሶስት ክትባቶችን እንዲያገኝ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል፡፡”

እነዚህ የክትባት መድሃኒቶች፣ መች እንደሚሰጡ ግልጽ አልሆነም፡፡ ባለፈው ሰኔው ውስጥ፣ በፕሬዚዳንት ባይደን ቃል ከተገባው፣ ወደ 500 ሚሊዮን ከሚጠጋው የክትባት መድሃኒት፣ 200 ሚሊዮን የሚሆነው የሚሰጠው ፣እኤአ፣ በ2021 መጨረሻ ሲሆን፣ 300 ሚሊዮን የሚሆነው ደግሞ እኤአ፣ በ2022 አጋማሽ ላይ ይላካል፡፡

ባይደን በተጨማሪም፣ በዓለም ላይ እነዚህን ክትባቶች፣ በየሰዎች ክንድ ላይ ለማሳረፍ እንዲረዳ፣ 750 ሚሊዮን ዶላር፣ እንዲሁም፣ በኮቪድ 19 ሳቢያ የሚደርሰውን ሞትና የቫይረሱን ተላላፊነት ለመቀነስ፣ ወደ 1.4 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡

ሰብአዊ ድርጅቶች፣ ተጨማሪ ክትባቶች መሰጠታቸውን በደስታ የተቀበሉ ቢሆንም፣ ለጋሾቹ በራሳቸው መንገድ ብቻ መለገስ አይኖርባቸውም ይላሉ፡፡

የድንበር የለሽ ሀኪሞች ድሬክተር ኬት ኤልደር እንዲህ ይላሉ

ልገሳዎቹ የሚካሄዱት በለጋሾቹ መልካም ፈቃድ ነው፡፡ ያላቸው ተጠያቂነት ግን አነስተኛ ነው፡፡ ልክ እንደ ዩናትድ ስቴትስ ሁሉ፣ በበለጸጉ አገሮች እንደሚሰጡ ቃል የተገባላቸው መቶ ሚልዮን የክትባት መድሃኒቶች መኖራቸውን አይተናል፡፡ በአውሮፓ ያሉ አገሮች፣ ክትባቶቹን የሚያደርሱበት መጠን እጅግ በጣም በጣም ያነሰ ነው፡፡ ክትባቶቹን በሰዎች ክንድ ላይ ማሳረፍ የምንፈልገው አሁኑኑ ነው፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን፣ በመላው ዓለም፣ ለኮቪድ 19 ህሙማን የሚያስፈልገው የኦክስጅን እጥረት፣ ምርመራዎች፣ የነፍስ ወከፍ መከላከያዎችና፣ እንክብካቤ መስጫዎችን አስመልከቶ፣ ላሉት ችግሮች እልባት እንዲሰጥ፣ ለዓለም መሪዎች ጥሪ አድርገዋል፡፡

ሌላው የተነሳው አብይ ጉዳይ፣ ወደፊት የሚከሰቱ ወረርሽኞችን በሚመለከት ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለወረርሽኝ ዝግጁነት የሚውል፣ በዓለም ባንክ ስር የሚተዳደር፣ የፋይናንስ በጀትና ዘርፍ እንዲመደብ ጠይቃለች፡፡

ፕሬዚዳንት ካማላ ኻሪስ እንዲህ ይላሉ

እኛ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለዚህ ፈንድ መጀመሪያ፣ ቢያንስ 250 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል እንገባለን፡፡ ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትም ተጨማሪ 850ሚሊዮን ዶላር ጠይቀናል፡፡

ድንበር የለሽ ሀኪሞች እንደሚያስረዳው፣ ከታዳጊ አገሮች መካከል፣ የመጀመሪያውን ዙር ክትባት እንኳ ያገኙት፣ ከ2 ከመቶ ያነሱ ናቸው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ግን፣ 330 ሚሊዮን የሚሆን፣ መላውን ህዝቧን ለማስከተብ የሚያስችል፣ በቂ ክትባት ያላት ሲሆን፣ ከግማሽ ቢሊዮን በላይ የክትባት መድሃኒት ትርፍ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ለአረጋውያንና ሌላ የጤና ችግር ላለባቸው አሜሪካውያን የሚሆን፣ ተጨማሪ የማጠናክሪያ ክትባቶችን ለመስጠት፣ ባወጣቸው እቅድም፣ ትችት ቀርቦባታል፡

አስተዳደሩ ግን፣ የማጠናከሪያ ክትባቱን እየሰጠም፣ ዓለምን ማስተከብ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ይሁን እንጂ የግቡ ተግባራዊነት የሚወሰነው፣ በክትባት መድሃኒት አምራች ድርጅቶች አቅም መሠረት ነው፡፡

ከጋራ የፖለቲካ ተቋማቱ ማዕከል፣ ወይም ባይ ፓርቲዛን ፖሊሲ ሴንተር፣ አናንድ ፓሬክ የሚከተለውን ብለዋል

አሁን ያሉት የክትባት አምራች ድርጅቶች በተባለው መጠን የማምረት አቅም አላቸው? ያንንስ ለሁሉም እኩል በማዳረስ ማከፋፈል ይችላሉ? ወይስ ሌሎች እንዲያመርቱ የምናስችልበት የቴክኖሎጂ ሽግግር ወይም የአምራች ባለቤትነት ፈቃድ ማዛወር የምንችልበት አሰራር ይኖረናል? ሌሎች አምራች ድርጅቶችስ እዚህ ነገር ውስጥ ይገቡበታል? ስለዚህ ይህ ሁሉ ተግባራዊ የሚሆነው በግቡ ዙሪያ ባለ ስምምነት መሰረት ነው፡፡

አምራች ድርጅቶችን በማስገደድ፣ ክትባቱን ማፋጠን የሚቻልበት አንዱ መንገድ ቢኖር፣ TRIPS እየተባለ በሚታወቀው፣ በዓለም ንግድ ድርጅት የሚተዳደረውን የክትባት ቴክኖሎጂን ፈቃድ፣ ወይም የፓተንት ገደብ ነጻ ማድረግ ነው፡፡ የባይደን አስተዳደር፣ ባለፈው ግንቦት ከሌሎች 100 አገሮች ጋር የገደቡን መነሳት እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዓለም ንግድ ድርጅት ውስጥ እየታሸ ያለው ጥያቄ፣ የሁሉንም አባላት ድጋፍ ሳይገኝ ማለፍ አይችልም፡፡

የዋይት ሀውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ፣ ለቪኦኤ ሲናገሩ፣ ጉዳዩ ሊዘገይ እንደሚችል አስተዳደሩ ግምት አለው ብለዋል፡፡ አያይዘውም

“ይሁን እንጂ ይህ የምናተኩርበት አንድ ነገር ብቻ አይደለም፡፡ በዓለም ላይ የክትባቱን ስርጭት በመጨመር ላይም እያተኮርን ነው፡፡ አገሮች የክትባት የማምረት አቅማቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስፈልጋቸው ነገር በሙሉ የተሟላላቸው መሆኑን ለማረጋገጥ አብረናቸው እየሠራን ነው፡፡” ብለዋል፡፡

በአራቱ አገራት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ህንድ፣ ጃፓንና አውስትራሊያ ወይም ኳድ እየተባለ የሚጠራው ቡድን አባል አገራት፣ ነገ አርብ በሚካሂደው ጉባኤ፣ የክትባቱ ጉዳይ ይነሳል፡፡ እኤአ በ2022፣ ከጃፓንና ከዩናይትድ ስቴትስ በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ጭምር፣ በህንድ፣ 1 ቢሊዮን የክትባት መድሃኒቶችን ለማምረት በተገባው ቃል ዙሪያ፣ ያለውን አፈጻጸም የሚመለከት ይሆናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ ካለፈው መጋቢት ወር ወዲህ፣ በዩናይትድ ስቴትስ በየእለቱ በኮቪድ 19 የሚሞቱ ሰዎች አማካይ ቁጥር 1ሺ900 ደርሷል፡፡ ከእነዚህ መካከል፣ ምንም እንኳ ክትባቱ ነጻና ዝግጁ መሆኑ ቢታወቅም ክትባቱን መውሰድ ያልፈለጉ 71 ሚሊዮን አሜሪካዊያን እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG