በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምዕራብ ወለጋ እና ካማሽ ዞኖች መካከል ለወራት የተቋረጠው የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ


በምዕራብ ወለጋ እና ካማሽ ዞኖች መካከል ለወራት የተቋረጠው የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:37 0:00

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞንና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ካማሽ ዞን መካከል፣ ለአራት ወራት ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተጀመረ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የካማሽ ዞን ኮምዩኒኬሽንስ መምሪያ ሓላፊ ገለጹ።

ስለ ጉዳዩ፣ ለአሜሪካ ድምፅ የተናገሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች፣ በጸጥታ ኃይሎች እጀባ እየገቡ እንደኾነ ገልጸው፣ እጥረት መኖሩንም አመልክተዋል። የዞኑ ኮምዩኒኬሽንስ መምሪያ በበኩሉ፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመሩን አረጋግጦ፣ አሁንም ቀሪ ተግባራት መኖራቸውን አስታውቋል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ካማሽ ዞኖች መካከል፣ ለበርካታ ወራት ተቋርጦ የቆየው የትራንስፖርት አገልግሎት እንደተጀመረ፣ የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በአካባቢው በነበረው የጸጥታ ችግር፣ ለአራት ወራት ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት፣ ባለፈው ሳምንት ውስጥ እንደተጀመረ፣ በስልክ የተናገሩት አቶ ግርማ ጀርሞሳ የተባሉ የካማሺ ነዋሪ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦችን ማስገባትም መጀመሩን አመልክተዋል።

ለደኅንነታቸው ስጋት ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላዋ የካማሽ ነዋሪ፣ የፍጆታ ሸቀጦቹ መግባት ቢጀምሩም፣ አሁንም እጥረት እንዳለ አልሸሸጉም።

እርሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም ነዋሪዎች፣ ለወባ በሽታ እየተጋለጡ እንደኾኑ የገለጹት አስተያየት ሰጪዋ፣ የሕክምና ቁሳቁሶች እና መድኃኒት እንደ ፍጆታዎቹ ወደ ካማሽ ባለመግባታቸው፣ መጪውም ክረምት ከመኾኑ አንጻር በእጅጉ እንደተቸገሩ ተናግረዋል።

የካማሽ ዞን ኮምዩኒኬሽንስ መምሪያ ሓላፊ ተወካይ አቶ ጀርሞሳ ተገኝ፣ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች፣ ባለፈው ሳምንት ሰኔ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ከምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ካማሽ በመንግሥት ኃይሎች እጀባ መግባት መጀመራቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ለአራት ወራት ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት መጀመሩ፣ ለኅብረተሰቡ ጊዜያዊ መፍትሔ እንደኾነም የገለጹት አቶ ጀርሳሞ፣ የእጀባ አገልግሎቱ፣ መንገዱ ከስጋት ነፃ እስኪኾን ድረስ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡

በተለይ፣ ከወባ በሽታ መድኃኒት እጥረት ጋራ ተያይዞ ለሚነሣው ቅሬታ፣ ችግሩን ለመፍታት የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ አቶ ጀርሞሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተቋርጦ የነበረው፣ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊትን ማስፈራሪያ እና ዝርፊያ በመስጋት እንደነበረ፣ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ነጋዴዎች ቢገልጹም፣ የሸማቂ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ ተጠይቀው፣ ታጣቂዎቻቸው የዘጉት መንገድ እንደሌለና ዝርፊያም እንደማይፈጽሙ ጠቅሰው ማስተባበላቸው ይታወሳል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰሎሞን ታምሩ በበኩላቸው፣ የመንግሥት ኃይሎች ወደ አካባቢው እንደሚሠማሩና አገልግሎቱም እንደሚጀመር፣ ቀደም ሲል ያስታወቁ ቢኾንም፣ አሁን የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከመጀመሩ ጋራ ተያይዞ፣ ከዞኑ ባለሥልጣናት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።

XS
SM
MD
LG