“የአማራ ተወላጆች ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉት በበታች አመራሮች ግብታዊ እርምጃ ነው” በማለት የተፈናቀሉት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል ፕሬዚደንት አቶ አህመድ ናስር ጥሪ ማቅረባቸውን ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው የረቡዕ ዕትሙ ዘግቧል።
ሪፖርተር ጋዜጣ እንደሚመለሱ ለይቶ የጠቀሰው ከቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል ካማሺ ዞን ያሶ ወረዳ የተፈናቀሉትን ዜጎች ነው።
ከቤንሻንጉል-ጉምዝ የሚፈናቀሉትን የአማራ ተወላጆች ጉዳይ በመከታተል ላይ የሚገኙት የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ የተፈናቀሉ ዜጎች ከፍኖተ ሠላም ከተማ በ21 አውቶቡሶች ተሳፍረው እንዲመለሱ መደረጉን አረጋግጠውልናል።
ዛሬም ወደ ክልል መስተዳደሩ ፕሬዚደንት አቶ አህመድ ናስር ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ መልስ አላገኘም፡፡
ትዝታ በላቸው ተፈናቃዮችን አነጋግራለች፡፡ ጥቃት እንዳይደርስባቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀዋል፡፡
ትዝታ በቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል የአማሮችን መፈናቀል በመከታተል ላይ የሚገኙ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት - መኢአድ ዋና ፀሐፊንም አነጋግራለች፡፡
የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ እንዲፈናቀሉ የሚደረጉ ዜጎች ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ንብረታቸው ተመልሶላቸው፣ ወደየቀያቸው ተመልሰው መኖር እንዲችሉ መንግሥት እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ገልፀውልናል።
ሪፖርተር ጋዜጣ በዛሬው /የረቡዕ፣ መጋቢት 2/2005 ዓ.ም/ ዕትሙ ይዞት በወጣው ዘገባ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አሕመድ ናስር “ኪራይ ሰብሳቢ የበታች አመራሮች በፈጠሩት ችግር የተፈናቀሉ 1 ሺህ 346 አባ ወራዎች ወደ ሥፍራው እንዲመለሱ ጥሪ ቀርቧል” ማለታቸውን ጠቅሷል።
ጥሪው የክልሉን ተፈናቃዮች ሁሉ ይጠቀልል እንደሆነና የተፈናቀለው ሰው ቁጥርም እስካሁን ግልፅ አይደለም።
ፕሬዚደንት አህመድ ናስር ካሁን ቀደም ለቪኦኤ በሰጡት ቃለ ምልልስ ከመተከል ዞን ቡለን ወረዳ አስራ ዘጠኝ ቀበሌዎች ስለ ተፈናቀሉ 5000 ሺህ ሰዎች ሲጠየቁ ቦታው ለከተማ ምሥረታ ይፈለጋል ማለታቸው አይዘነጋም።
ዘገባውን ያዳምጡ