የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ትላንት ማታ ያረፉት ባደረባቸው ህመም በውጭ ሀገር ሕክምና ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ መሆኑን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሥርዓተ ቀብር የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ብሔራዊ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን የአገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ በረከት ስምዖን ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሥርዓተ ቀብር እስከሚፈጸም ድረስ በመላ አገሪቱ ብሔራዊ ሐዘን ሆኖ ይቆያል።
በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሠረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን በሙሉ ሥልጣን የመምራት ኃላፊነት መረከባቸው ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ በሚካሄድበት ወቅት፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ምርጫ የሚደረግ ሲሆን፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፓርቲውንና የመንግስት ኃላፊነትን ይዘው የሚቀጥሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሞት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሚፈጠር ምንም አዲስ ነገር እንደማይኖር የገለጹት አቶ በረከት፥ «ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤» ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዓለም አቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያንና አፍሪቃን በመወከል ለሰላምና መረጋጋት በትጋት ሠርተዋል፤ ተብለው በውጭ ይወደሳሉ። ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የሚከራከሩ ቡድኖች ግን ነፃ ሚዲያ ማፈንን ጨምሮ በበርካታ የመብት ጥሰቶች አጥብቀው ይተቿቸዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታዩት በሰኔ ወር መገባደጂያ ከሃምሳ ቀናት በፊት ሲሆን፥ የጤንነታቸው ይዞታና ያሉበት ቦታ በውል ሳይታወቅ ለወራት ሲያወዛግብ መቆየቱም የሚታወቅ ነው።
አቶ መለስ ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣበት ከ1983ዓም አንስቶ ኢትዮጵያን መጀመሪያ በፕሬዝዳንትነት፥ ኋላም በጠቅላይ ሚንስትርነት ከሃያ ዓመት በላይ መርተዋል።
* * * የዝግጅት ክፍላችን የምሽቱን ሙሉ የአንድ ሰዓት ፕሮግራም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዜና እረፍት፥ የሕይወት ታሪካቸውና ትንታኔዎች ያውላል።