በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሃምሣኛ ዓመታዊ ሪፖርቱን አወጣ


አምነስቲ ኢንተርናሽናል
አምነስቲ ኢንተርናሽናል

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት “የመሪዎች መብቶችን ያለማስከበር ውድቀት ዓለምአቀፋዊ ሆኗል” አለ።

“የኢትዮጵያና የርዋንዳ ፈላጭ ቆራጭ መንግሥታት ተቃዋሚዎችን እያፈኑና ጋዜጠኞችን እያሣደዱ ሰብአዊ መብቶችን ከማክበር ይልቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ እንዲተኮር እያደረጉ ነው” ይላል አምነስቲ እንተርናሽናል።

“ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በአማካይ እስከ አስራ አንድ ነጥብ ባስቆጠረ የኢኮኖሚ ዕድገት 83 ሚሊዮን ሕዝቧን ከድህነት ለማውጣት እየሞከረች ነዉ፥ ላለፉት ሃያ ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው ፈላጭ ቆራጭ ገዥ ፓርቲዋ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የወጡትን የሚሌንየሙን የልማት ግቦች በብሔራዊ የዕድገት ፖሊሲው ለማካተት እየጣረ ነው። ሆኖም እነዚህ ሁሉ መሻሻሎች የሰብአዊ መብቶች ዋጋ የተከፈሉባቸው ናቸው” ብለዋል የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ኤርዊን ቫን ደር ቦርት፡፡

ድርጅቱ በዓመታዊ ዘገባው በአገሪቱ ውስጥ አሣሣቢ ያላቸውና ያሠመረባቸው የመብቶች ጥሰቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን መብት የሚገድብው ሕግ፣ እንዲሁም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ጋዜጠኞች መታሠራቸውን ነው።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል “እንደ ኢትዮጵያው ሁሉ የርዋንዳም ጉዳይ አሣሣቢ ነው” ይላል በዓመታዊ ሪፖርቱ። በፕሬዚደንት ፖል ካጋሜና በፓርቲአቸው የአርበኝነት ግንባር (Patriotic Front) ጥብቅ አመራር ሥር ርዋንዳም ባለፉት ዓመታት የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝግባለች። የዓለም ባንክ ርዋንዳን “ከተሻሻሉ አሥር የዓለም ኢኮኖሚዎች አንዷ” ብሏታል ባለፈው ዓመት። ዘንድሮ “ንግድ ለመጀመር ቀላል ከሆነባቸው ሦስት የአፍሪቃ አገሮች አንዷ” ተብላለች ርዋንዳ። “ሆኖም - ይላል አምነስቲ ኢንተርናሽናል - ርዋንዳ ያለምንም ፍትሐዊ ሂደት የመንግሥት ተቺዎችን ማሠር፤ ኢፍትሃዊ የሆኑ ውሣኔዎችን ተቃዋሚዎች ላይ መፍረድ፣ ጋዜጠኞችን ማሣደድና ማሠር ቀጥላለች።

ከኢትዮጵያና ርዋንዳ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት ስለዓለም ያወጣው ዘገባ ላይ ስናተኩር የአውሮፓዊያን 2011 ዓመትን “መረጋጋት ያልታየበት” ሲል ይገልፃል።

በበጎ ገፅታው ሲታይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች በየአደባባዩ ወጥተው መብቶቻቸውን ጠየቁ፤ ከፊሉም ጥያቄአቸውን በማስመለስ ድል ተቀዳጁ፣ በተለይም የመካከለኛው ምሥራቅና የሰሜን አፍሪቃ ህዝቦች ባካሄዱት ሠላማዊ “መብታችንን ካልመለሳችሁ እምቢታ” ከብረት በጠነከረ ክንድ ለዓመታት የገዟቸውን መሪዎች ተፈታተኑ፤ ከሥልጣንም አወረዱ።

ሆኖም ህዝቡ የታገለላቸውን መብቶች እውን የሚያደርጉለት ጠንካራ ብሔራዊ ወይም ዓለምአቀፍ መሪዎች አላገኘም - ብሏል አምነስቲ ኢንተርናሽናል፡፡

በሎንዶን ቢሮው የድርጅቱ የዓለምአቀፍ ሕግና ፖሊሲ ኃላፊ ዊንዲ ብራውን “በየአገሮቹ የፓለቲካ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ የሕዝቡን ተቃውሞ ለመበተን ኃይል እንደተጠቀሙ፣ ዓለምአቀፍ መሪዎች ደግሞ ሽርክናቸውን ወይም የገንዘብ ጥቅም በማስቀደም የሰብዓዊ መብቶች ከበሬታን ቸል ብለዋል” ይላሉ።

“ከዚያም በላይ - ይላል የአምነስቲ ሪፖርት - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት በዚህ ባለፈው ዓመት ቀውጢ ጊዜ፣ የተዳከመና ለቆመለት ዓላማ የማይመጥን ሆኖ ተገኝቷል” ብሎታል።

አምነስቲ እንተርናሽናል በዘንድሮው የሰብአዊ መብቶች ሪፖርቱ የፊታችን ሐምሌ በኒው ዮርክ በሚካሄድ ጉባዔ ላይ በመሣሪያ ሽያጭ ቁጥጥር ላይ እንዲተኮር ጠይቋል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የመሣሪያ ቁጥጥር ኃላፊ ብራያን ዉድስ “ወደ ሌሎች አገሮች በንግድ የሚላኩ መሣሪያዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሊውሉ እንደሚችል ታውቆ ጭነቶቹ እንዲቆሙ መደረግ አለባቸው” ብለዋል።

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG