በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዐማራ ክልል ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ሥርጭት አርሶ አደሩ የበለጠ ተጎጂ እንደሚኾን ተጠቆመ


ፎቶ ፋይል፦ ባህር ዳር ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ ባህር ዳር ከተማ

በዐማራ ክልል፣ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች ሥርጭት አሳሳቢ እየኾነ እንደመጣ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ኮሚሽኑ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ፣ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ሐሰተኛ የኢትዮጵያ እና ከ98ሺሕ በላይ የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ኖቶችን በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ ገልጿል፡፡

በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶቹ ተጎጂ የኾነው፣ በተለይ በገጠሩ የሚገኘው የኅብረተሰብ ክፍል እንደኾነ፣ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶቹ ሥርጭት፥ “የዋጋ ንረትን በማባባስ እና የፖሊሲ ቀረጻን በማዛባት፣ ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖን ያስከትላል፤” የሚለው፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር በበኩሉ፣ ዘመናዊ የግብይት ሥርዐት እንዲስፋፋ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ሓላፊ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ወልዴ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንዳስታወቁት፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት፣ በክልሉ፥ 16 ሚሊዮን የብር፣ እንዲሁም 98ሺሕ የዶላር የሐሰት ኖት በቁጥጥር ሥር ውሏል፡፡ የሐሰተኛ ገንዝብ ሥርጭቱ፣ ባሕር ዳርንና አካባቢውን ጨምሮ፣ በሰባት ዞኖች በስፋት እየተስተዋለ እንደኾነ አስረድተዋል፡፡

በዐማራ ክልል ሐሰተኛ የገንዘብ ኖት ሥርጭት አርሶ አደሩ የበለጠ ተጎጂ እንደሚኾን ተጠቆመ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:39 0:00

በሰሜን፣ በምእራብና በደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ በጎንደር ከተማ አስተዳደር፣ በባህርዳር ከተማ አስተዳደርና ዙሪያው፣ በምዕራብና በምስራቅ ጎጃም፣ በሰሜን ወሎና በአዊ ብሔረሰብ የሃሰት የገንዘብ ዝውውሩ በስፋት እንደሚስተዋል ረዳት ኮሚሽነሩ አብራርተዋል፡፡ ችግሩ በስፋት የሚስተዋለውም በአርሶ አደሩ የግብይት ወቀት እንደሆነ አክለው ጠቁመዋል፡፡

በተለይ የሐሰተኛ ብር ኖቶቹ፣ በስፋት አገልግሎት ላይ ሲውሉ የሚታዩት፣ በቁም ከብት ሽያጭ እና በአርሶ አደሩ የገበያ ልውውጥ ላይ ነው፡፡ በዚኽም፣ አርሶ አደሩ ለችግር እየተዳረገ እንደሚገኝ፣ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊለያቸውና የሐሰተኛና ትክክለኛ የገንዘብ ኖቶቹን ምልክት አውቆ ሊከላከል ባለመቻሉ ሃብቱን በሐሰተኛ ገንዘብ እያጣ ለድህነት እየተዳረገ ነው ይላሉ፡፡

እንደ ረዳት ኮሚሽነር ክንዱ ገለጻ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ፣ በሐሰተኛ የብር ኖት ሥርጭት የተጠረጠሩ 89 ሰዎች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሞያዎች ማኅበር፣ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር አደም ፈቶ፥ የሐሰተኛ ብር ሥርጭቱ፣ ኢኮኖሚውን በሁለት መንገድ እንደሚጎዳው ያብራራሉ፡፡ በቀዳሚነት የጠቀሱትም፣ የዋጋ ንረትን በማባበስ ያለውን ተጽእኖ ነው፡፡

ብዙ የብር ኖት በሕጋዊም ኾነ በሐሰተኛ መንገድ ወደ ገበያ ከገባ የዋጋ ግሽበት ይባባሳል፡፡ አሁን ያለው የዋጋ ግሽበት መጠን 30 በመቶ ደርሷል በዚህ ሁኔታ ሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ገበያ ውስጥ ከገባ የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን እንደሚችል ዶክተር አደም ስጋታቸውን ይገልጻሉ ፡፡

የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀረጻን እንደሚያዛባ፣ ያመለከቱት ዶክተር አደም፣ በሰሜኑ ጦርነት እና ጦርነቱን ተከትሎ በተከሠተው የዋጋ ንረት፣ በገጠራማው የአገሪቱ አካባቢ የሚኖሩ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሸማቾች እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አምራቾች፣ ለሐሰተኛ ብር ኖት በስፋት ተጋላጭ እንደኾኑ፣ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ይገልጻሉ፡፡

አካባቢው በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር፣ በሰላም እጦት አብዛኛው አርሶ አደር ሳያመርት ቆይቷል፤ያለችውን አንጡራ ሃብት በሐሰተኛ ብር ካጣ ደግሞ ለከፋ ችግር ይዳረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐሰተኛ ብር ይዞ መገኘት ወንጀል በመሆኑ እስከመጉላላት ይደርሳል”

“አካባቢው በማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር፣ በሰላም እጦት አብዛኛው አርሶ አደር ሳያመርት ቆይቷል፤ያለችውን አንጡራ ሃብት በሐሰተኛ ብር ካጣ ደግሞ ለከፋ ችግር ይዳረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐሰተኛ ብር ይዞ መገኘት ወንጀል በመሆኑ እስከመጉላላት ይደርሳል” ብለዋል፡፡

ትክክለኛውን የገንዘብ ኖት ከሐሰተኛው ለመለየት የተቀመጡ ማሳያዎች ቢኖሩም፣ በቀላሉ ለማስረዳት የሚያዳግቱ ውስብስብ በመኾናቸው እና በመረጃው የተደራሽነት ችግር ምክንያት፣ የገጠሩ ነዋሪ የበለጠ ተጎጅ ሊኾን እንደሚችል፣ ዶር. አደም አስገንዝበዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ፥ ዘመናዊ እና ምቹ አሠራሮችን እየቀረጸ፣ የገጠሩን ማኅበረሰብ ተደራሽ በማድረግ፣ የሐሰተኛ ብር ኖት ሥርጭትን መከላከል እንደሚኖርበት፣ የሞያ ማኅበሩ ከፍተኛ ተመራማሪ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡

ስለ ጉዳዩ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስተያየት ለማግኘት ጥረት እያደረግን ሲኾን፣ እንደተሳካልን ይዘን የምንመለስ ይኾናል፡፡

/የዚህ ዘገባ ሙሉ ይዘት በተያያዘው የድምፅና ምስል ፋይል ውስጥ ይገኛል/

XS
SM
MD
LG