በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደንበጫ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች ተቃውሞ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ


በደንበጫ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች ተቃውሞ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:07 0:00

በምዕራብ ጎጃም ዞን ደንበጫ፣ ጅጋ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች፣ ትላንትና እና ከትላንት በስቲያ በነበረ የተኩስ ልውውጥ፣ የሦስት ሰዎች ሕይወት እንዳለፈና ከ20 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን፣ የደንበጫ እና ፍኖተ ሰላም ሆስፒታሎች ሥራ አስኪያጆች ገለጹ፡፡

የየአካባቢው ነዋሪዎች፣ ዛሬ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት አስተያየት፣ በሁለቱ ከተሞች፣ ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት፣ የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎችን መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

ትላንት፣ ከዐዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር የሚወስደው ዋናው መንገድ በመዘጋቱ፣ ትራንስፖርት ተስትጓጉሎ እንደነበርና ዛሬ መከፈቱን፣ እንዲሁም በፍኖተ ሰላም ከተማ ሰልፍ ወጥተው በነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ አንድ ሆቴል መውደሙን፣ ነዋሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በበኩሉ፣ ካለፈው እሑድ ምሽት ጀምሮ፣ በዞኑ ደንበጫ፣ ጅጋ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች፣ ተከሥቶ የነበረው አለመረጋጋት፣ ዛሬ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን አስታውቋል፡፡

ባለፈው እሑድ እና ትላንት ሰኞ፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን በደንበጫ እና በፍኖተ ሰላም ከተሞች በነበሩ ግጭቶች፣ ሰዎች መሞታቸውንና መቁሰላቸውን፣ የደንበጫ እና የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሥራ አስኪያጆች፣ ዛሬ ለአሜሪካ ድምፅ አረጋግጠዋል።

የደንበጫ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዐዲሱ ፍቅሬ፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ ማታ፣ በጥይት ተመትተው የቆሰሉ ሰዎች፣ ወደ ሆስፒታሉ መግባታቸውንና በደረሰባቸው ጉዳት የተነሣ፣ ሰዎች ለኅልፈት መዳረጋቸውን ተናግረዋል።

በደንበጫ ከተማ፣ መናኸሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ከትላንት በስቲያ እሑድ አመሻሽ በሥፍራው ነበርኹ፤ ያሉ፣ ስማቸውን በምሥጢር እንድንይዝ የጠየቁን አንድ ነዋሪ፣ በዕለቱ የነበረውን ኹኔታ ለአሜሪካ ድምፅ እንዲህ አብራርተዋል።

ትላንት ሰኞ ከቀትር በኋላ፣ በጥይት ተመትተው ወደ ሆስፒታል የገቡ ሰዎች እንደነበሩና ከእነዚኽም መካከል አንድ ሰው እንደ ሞተ የገለጹልን ደግሞ፣ የፍኖተ ሰላም ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ አቶ ማናየ ጤናው ናቸው፡፡

የከተማው ነዋሪዎች፥ መንግሥት፣ በአካባቢው የሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት እንዲያቆም የሚጠይቅ ሰልፍ ተደርጎ እንደነበርና በሰልፉ ላይ ግጭት መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

በሰልፉ ወቅት የተኩስ ልውውጥ እንደነበር የገለጹት እኚኹ የከተማው ነዋሪ የኾኑ አስተያየት ሰጪ፣ ልውውጡ በማንና በእነማን መካከል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

የምዕራብ ጎጃም ዞን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሓላፊ አቶ ዘመኑ ታደለ በበኩሉ፣ ካለፈው እሑድ ምሽት ጀምሮ፣ በዞኑ ደንበጫ፣ ጅጋ እና ፍኖተ ሰላም ከተሞች፣ ተከሥቶ የነበረው አለመረጋጋት፣ ዛሬ ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት የሰላም እና ጸጥታ ቢሮም፣ በሚያዝያ ወር ባወጣው መግለጫ፣ የሕግ ማስከበር ርምጃው፣ አጥፊዎች ለሕግ እስኪቀርቡ ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል፤ ማለቱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል፣ በዐማራ ክልል ምክር ቤት፣ የዐማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ ተመራጭ የኾኑ 13 የሕዝብ እንደራሴዎች፣ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት፣ ያለክልሉ ምክር ቤት የእገዛ ጥያቄ በሕግ ማስከበር ስም ወደ ዐማራ ክልል ያስገባውን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ እንዲያስወጣ ጠይቀዋል።

ምንም እንኳን መንግሥት፣ በክልሉ እየሰወደ ያለው ርምጃ፣ ሕግ የማስከበር እንደኾነ ቢገልጽም፣ የዐማራ ክልል ምክር ቤት አባል የኾኑ የአብን ተመራጮች ግን፣ ርምጃው፥ ሕግን የተከተለ አይደለም፤ ሲሉ ተቃውመዋል። የፌደራል መንግሥት፣ የመከላከያ ሠራዊቱን ወደ ክልሉ ያስገባው፣ የዐማራ ክልል ምክር ቤት፣ እገዛውን ሳይጠይቅ በመኾኑ፣ ይህም፣ ርምጃውን ሕገ ወጥ እንደሚያደርገው አስረድተዋል፡፡ ይልቁንም፣ እየተወሰደ ያለው ርምጃ፥ በክልሉ ላይ የተከፈተ ጦርነት ነው፤ ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG