በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ ከተራቡ ሰዎች በተጨማሪ ሶማሊያዊያን ስደተኞች እርዳታ ይሻሉ


በሶማሊያ ርሃቡ የጠናባቸው ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ በማምራት ላይ ናቸው
በሶማሊያ ርሃቡ የጠናባቸው ድንበር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያና ኬንያ በማምራት ላይ ናቸው

የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በ60 አመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ተመትተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በኬንያ 3.5 ሚሊዮን ፥በኢትዮጵያ 4.5 ሚሊዮን እንዲሁም በሶማሊያ 2.9 ሚሊዮን ህዝብ ለዚሁ አደጋ ተጋልጧል፡፡ በአደጋው የተጋለጠውን ህዝብ ለመታደግ ከፍተኛ እርዳታ እንደሚያስፈልግ WFP ገልጿል።

በአፍሪቃ ቀንድ በተከሰተው ድርቅ ለከፋ አደጋ የተጋለጡ ወገኖችን ለመድረስ የያዘውን ጥረት መጨመሩን የተባበሩት መንግስታት ድርግት የምግብ ፕሮግራም WFP አስታወቀ።

የአሜሪካ ድምጹ ጋቢ ጆስሎ ከናይሮቢ ባጠናቀረው ዘገባ እንደጠቆመው፤ የተጎዱትን ወገኖች በአስቸኳይ ለመድረስ የሚያስፈልገውን እርዳታ ለማሟላት ድርጅቱ ለተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ጥሪ አቅርቧል።

ይህን ያስታወቁት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስነህዝብ የስደተኞችና የፍልሰት ጉዳይ ጽ/ቤት ም/ል ረዳት ጸሃፊ ዶ/ር ሪበን ብርጌቲ ናቸው፡፡ ከዶናልድ ቡዝ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና ከዶናልድ ስታይበርግ የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ተራዲኦ ድርጅት ም/ል አስተዳዳሪ ጋር በጋራ ትላንት አመሻሹ ላይ በሰጡት መግለጫ ሶማሊያ ውስጥ እየተባባሰ በመጣው ድርቅና ጦርነት የተነሳ ብዙ ሱማሊያውያን ወደኢትዮጵያና ኬንያ እየተሰደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ረዳት ጸሃፊው በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ በዶሎ አዶ የሰደተኞች ካምፖች የተመለከቱትን ገጽታ አስረድተዋል፡፡ “ዛሬ በዶሎ አዶ የስደተኞች ካምፕ የሚገኙ የስደተኞች ቁጥር ወደመቶ ሺህ ይጠጋል፡፡ የስደተኞች ጎርፍ በዚሁ ከቀጠለ በአመቱ መጀመሪያ ላይ በእጥፍ ይጨምራል፡፡ ወደ ካምፑ የሚመጡትም በአካልና በጤና የተጎሳቆሉ ናቸው፡፡ በአልተመጣጠነ ምግብ ምክንያት የሚደርሰው ጉዳትም ከ45 እስከ 50 በመቶ ይሆናል፡፡ ይህ በህጻናቱ መካከል 20 በመቶ ይደርሳል፡፡”

በሱማሊያ ያለው ግጭት ድርቁን እንዳባባሰውም ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ያዩትን ረዳት ጸሀፊ ሲናገሩም “ከሞቃዲሾና ከሌሎች አካባቢዎች ከ4- 10 ቀን ተጉዘው የመጡ ስደተኞችን አነጋግረናል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው በእቅፋቸው ላይ ይሞታሉ፡፡ ሁሉም እንደሚሉት በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ ምግብ ማግኘት ባለመቻላቸውና በአገሪቱ ያለው ጦርነት ለስደት ዳርጓቸዋል፡፡”

አሁን በምስራቅ አፍሪካ የደረሰው ድርቅ በ60 አመታት ውስጥ ያልታየ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡ ይህ መቅሰፍት እንደሚመጣም በአሜሪካ መንግስት አስቀድሞ ይታወቅ እንደነበረ የአሜሪካ አለም አቀፍ የልማት ተራዲኦ ድርጅት ም/ል አስተዳዳሪ ዶናልድ ስታይበርግ ተናግረዋል፡፡ ይህ የታወቀውም በሳተላይትና ምድር ላይ በተገኙ መረጃዎች ሳይንሳዊ ትንታኔ መሰረት ነው፡፡ የተፈራው ድርቅም ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ መከሰት ጀመረ፡፡ ዶናልድ ስታይምበርግ “እነዚህ የአስቸኳይ ሁኔታዎች በእርግጥም ተከሰቱ፡፡ በጥቅምት 2003 ዓ.ም. በሶማሊያ የደረሰውን ቀውስ ይፋ አደረግን፡፡ አሁንም በታህሳስ በኬንያ የተፈጠረውን ተመሳሳይ ሁኔታ ይፋ አደረግን፡፡ በየካቲት ደግሞ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን አደጋ አሳውቀናል፡፡”

በአሁኑ ጊዜ በምስራቅ አፍሪካ እርዳታ የሚሹ ዜጎች ቁጥር በሚሊዮኖች መቆጠር ጀምሯል፡፡ ስታይምበርግ በዝርዝር ሲናገሩ “በተከሰተው ቀውስ ሳቢያ ጉዳቱ የተጋረጠበትን ህዝብ ቁጥር ታውቃላችሁ፡፡ በኬንያ 3.5 ሚሊዮን ህዝብ ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርጓል፡፡ በኢትዮጵያ 4.5 ሚሊዮን ህዝብ ለተመሳሳይ አደጋ ተዳርጓል፡፡ በሶማሊያ ደግሞ 2.9 ሚሊዮን ህዝብ ለዚሁ አደጋ ተጋልጧል፡፡ 60 በመቶ የሚሆነው ህዝብ በግጭት ቀጣና ውስጥ ስለሚገኝ እርዳታ ማግኘት አይችልም፡፡ በተጨማሪም በኡጋንዳ 600 ሺህ በጅቡቲ 120 ሺህ ህዝብ ለድርቅ አደጋ ተጋልጧል።”

በአሁኑ ጊዜ በዶሎ አዶ የሱማሊያ ስደተኞች ጣቢያዎች ውስጥ በየቀኑ ከ2-3 ወይም ከ10 ሺዎች ውስጥ 7 ህጻናት እንደሚሞቱ ተናግረዋል። የዶሎ አዶ ጣቢያዎች ከአሜሪካ ባለስልጣናት በተጨማሪ በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ተወካዮች፥ የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞችና ስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር ተወካዮች፥ የዩናይትድ ኪንግደም አለማቀፍ ክፍል፥ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች እንዲሁም የሲዊዲንና የጃፓን መንግስት ተወካዮች ጎብኝተዋቸዋል።

XS
SM
MD
LG