በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኡሙሩ ወረዳ አምስት አርሶ አደሮች በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ


በኡሙሩ ወረዳ አምስት አርሶ አደሮች በታጣቂዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:40 0:00

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ዞን ኡሙሩ ወረዳ፣ የእርሻ ሥራ በማከናወን ላይ የነበሩ አምስት አርሶ አደሮች፣ በታጣቂዎች መገደላቸውን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ለአሜሪካ ድምፅ ገለጹ። ነዋሪዎቹ፣ ጥቃቱ የተፈጸመው፣ “የዐማራ ታጣቂዎች” ብለው በጠሯቸው ኃይሎች እንደኾነ ገልጸዋል።

በወረዳው ውስጥ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት፣ በአካባቢው የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆችን፣ በስልክ አግኝተን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ በኩል፣ የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ፣ በተጠቀሰው አካባቢ የሚገኙ የዐማራ ተወላጆች፣ “ጥቃት ይደርስባቸዋል እንጂ ጥቃት ያደርሳሉ፤” የሚል እምነት እንደሌላቸው በመጥቀስ ውንጀላውን ተከላክሏል።

የዞኑ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ሓላፊም፣ “በአሙሩ፣ ንጹሐን ሰዎች በታጣቂዎች ስለመገደላቸው የሚያመላክት የተጣራ መረጃ አላገኘንም፤” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩ ወረዳ፣ የሲደን ቀበሌ ነዋሪ እንደኾኑ በስልክ የገለጹ፣ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ ባለፈው ሳምንት ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም፣ ከጃርቴ ጃርዳጋ ወረዳ የመጡ ታጣቂዎች፣ ንጹሐን ሰዎችን ገድለዋል፤ ሲሉ፣ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ገልጸዋል።

ነዋሪው እንዳሉት፣ “የተመቱት አምስት ሰዎች ናቸው። አራቱ ወንዶች ናቸው። አንደኛዋ ሴት ከልጇ ጋራ የተገደለች ናት። ጥቃቱንም ያደረሱት፣ የታጠቁ የዐማራ ጽንፈኞች ናቸው። የደቦ ሥራ ነበር፤ ቤቱን ከበው ነው ያየናቸው። በዚያው ምሽት ተመልሰው መጡና ንብረት ዘርፈው ሔዱ።”

ከጥቃቱ በኋላ፣ ከአካባቢው በመፈናቀላቸው፣ በአቅራቢያው በሚገኘው ኦቦራ በሚባል የወረዳው ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹልን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁን ግለሰብ፣ በታጣቂዎቹ ደርሷል፤ ያሉትን ጥቃት ሲያስረዱ፤ “ረቡዕ ጠዋት፣ የደቦው ቦታ ላይ በጋራ ኾነን የእርሻ ሥራ እየሠራን፣ ሁለት ሰዓት አካባቢ፣ ጽንፈኛ የሚባሉ የዐማርኛ ተናጋሪ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው፣ አምስት ሰዎችን ገድለዋል። ዱሬ ኢረና እና ልጃቸው፣ ከተማ

ያደታ፣ ደቾ ደረጀ እና ዓለማዮ ያደታ የሚባሉት፣ በዕለቱ በደቦው ቦታ ላይ ነው የተገደሉት። አብዲ ዱፌራ የተባለ ግለሰብን ታጣቂዎቹ ይዘውት ሔደዋል፡፡ ይኑር ይሙት አናውቅም፤” ብለዋል።

በአካባቢው የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆች፣ ራሳቸውን ከታጣቂዎች ጥቃት ሲከላከሉ፣ ጽንፈኛ እንደሚባሉ ከዚኽ ቀደም ሲገልጹ፣ ባለፈው ሳምንት፣ በአሙሩ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት ግን፣ በአካባቢው የሚኖሩ የዐማራ ተወላጆችን በስልክ አግኝተን ስለ ጉዳዩ ለመጠየቅ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።

በሌላ በኩል፣ የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ መኾናቸውን የገለጹና መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉት አቶ ኡመር ሽፋው፣ የዐማራ ተወላጆች ጥቃት ይደርስባቸዋል እንጂ፣ ጥቃት ያደርሳሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው በመግለጽ ውንጀላውን ይከላከላሉ፡፡

በዚኽ ጉዳይ የተጠየቁት፣ የዞኑ አስተዳደር እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ አብዲሳ ቀነኣ፣ “በአሙሩ፥ ንጹሐን ሰዎች በታጣቂዎች ስለመገደላቸው የሚያመላክት የተጣራ መረጃ አላገኘንም፤” ካሉ በኋላ፣ ጽንፈኞች የሚሏቸው ታጣቂዎች ግን ዘረፋ እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።

“ሲደን በተባለ ቦታ፣ በንጹሐን ሰዎች ላይ ግድያ ስለመፈጸሙ የሚያሳይ የተጣራ መረጃ የለኝም። ነገር ግን፣ ከጽንፈኞች ጋራ ተያይዞ ችግር እንዳለ ይታወቃል። በተለይ ከዐማራ የወጡ ነገር ግን የዐማራን ሕዝብ የማይወክሉና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ዝርፊያ የሚፈጽሙና የኅብረተሰቡን ከብቶች የሚዘርፉ ይታያሉ። ሕዝብን ከሕዝብ ጋራ ለማጋጨት የሚጥሩ አሉ። ይህን ለመቆጣጠር ደግሞ፣ መንግሥት እየሠራበት ይገኛል። በፊት፣ የሕዝብ መፈናቀል አስከትለው ነበር። ነገር ግን ሕዝቡ፣ ሲደን ወደተባለው ሥፍራ ተመልሷል። አልፎ አልፎ የሚታየውን ችግር ለመፍታትም፣ መንግሥት እየሠራ ነው። ሕዝቡ ወደ ልማቱ እየተመለሰ ስለመኾኑ መረዳት ያስፈልጋል። ችግሮቹን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት፣ በአገር ሽማግሌዎች በኩል እየተሠራ ነው፡፡”

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ሓላፊው አቶ አብዲሳ፣ “ሕዝቡ ወደ አካባቢው ተመልሶ የእርሻ ሥራውን እያከናወነ ነው፡፡ መንግሥት የጸጥታ ኃይሉን እስከ ቀበሌ በማሠማራት እና በሕዝቡ መካከል ውይይት በማካሔድ፣ እየተሻሻለ ያለውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እየሠራ ነው፤” ሲሉ ገልጸዋል።

የዐማራ ሕዝባዊ ግንባር የውጭ ድጋፍ ሰጪ ግብረ ኃይል ቃል አቀባይ አቶ ኡመር ግን፣ በአሁኑ ወቅት ጥቃት እየደረሰባቸው ያሉት የዐማራ ተወላጆች ናቸው፤ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን(ኢሰመኮ)፣ የክልሎች ክትትል እና ምርመራ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ኢማድ አብዱልፈታ፣ በኡሙሩ ወረዳ ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት፣ ኮሚሽናቸው ያውቅ እንደኾነ ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ፣ መረጃው እንዳላቸውና ያጣሩት ነገር ግን አለመኖሩን ተናግረዋል - “አሁን ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት፣ በአካባቢው ካለው ተጨባጭ ኹኔታ አንጻር፣ እንደ መረጃነቱ መረጃ ይኑረን እንጂ፣ ወደ ታች ወርደን ያጣራነው ነገር የለም፤” ብለዋል፡፡

አቶ ኢማድ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ የመንግሥትን ኃይሎች ጨምሮ ሌሎችም የታጠቁ ኃይሎች በሚያደርሱት ጥቃት፣ ንጹሐን ዜጎች ሕይወታቸውን እያጡ እንደኾነና ግጭት እንዲቆም በተለያዩ ጊዜያት ሲያሳስቡ እንደቆዩ አውስተዋል።

“በተደጋጋሚ ባወጣናቸው ሪፖርቶች እና መግለጫዎች ለማንሣት እንደሞከርነው፣ በኦሮሚያ ውስጥ ባለው ግጭት፣ በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በሚከሠቱ ግጭቶች፣ የመንግሥት ኃይሎችን ጨምሮ በተለያዩ ኹኔታዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት፣ በልዩ ልዩ ብሔር ንጹሐን ተወላጆች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ አሁንም እየፈጸሙ በመኾናቸው፣ ከቀደሙ የቀጠለና ዐዲስ ነገር አይደለም። ሰላም እንዲወርድና ጥቃቱ እንዲቆም፣ ለችግሩም መፍትሔ የሚኾን ውይይት እንዲካሔድ በተደጋጋሚ ስናሳስብ ቆይተናል።”

በሌላ በኩል ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ(UN-OCHA)፣ በኦሮሚያ ክልል፣ በተለይም በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞኖች ውስጥ የቀጠለው ግጭት፣ ለንጹሐን ሰዎች ግድያ እና መፈናቀል መንሥኤ ስለመሆኑ፣ ትላንት ባወጣው ሪፖርቱ ገልጿል።

በተለይም፣ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች፣ እንዲሁም በምሥራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ፣ ባለፉት በርካታ ቀናት በደረሰው ጥቃት፣ ንጹሐን ሰዎች መገደላቸውንና መፈናቀላቸውን፣ ማስተባበርያ ቢሮው ሲያመለክት፣ ከባለድርሻ አካላት እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋራ በመኾን፣ በደረሰው መፈናቀል ዙሪያ መረጃ ለማሰባሰብ እየሠራ እንደኾነ አስታውቋል።

በአካባቢው ካለው የጸጥታ ችግር አንጻር፣ የሰብአዊ ድጋፎች ተደራሽነት ውስን እንደኾነ በመግለጽ፣ ሰብአዊ ድጋፎችን ማድረስ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክቷል። የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮው፣ በአካባቢው ጥቃት ስለመድረሱ እንጂ፣ ጥቃቱ በማንና በእነማን ላይ እደደረሰ የጠቆመው ነገር የለም።

XS
SM
MD
LG