የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በኢትዮጵያ እንዲሰራጭ እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቆይተዋል።
አቶ መለስ ቪኦኤ በአሜሪካ እንዲያሰራጭ በህግ አይፈቀድለትም፤ እኛም በተለይ አማርኛ አገልግሎቱን በኢትዮጵያ እንዲያሰራጭ አንፈቅድም ሲሉ ይደመጣሉ።
የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ በ1935 በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት ከተቋቋመ ወዲህ የተለያዩ ተቋማዊ ሃላፊነቶች ነበሩበት።
የዜና ማሰራጫው አሁን ያለበትን ህልውናና ተግባራዊ ቅርጽ የያዘው ከ1940 ጀምሮ በየጊዜው በወጡ ህጎች ነው።
በሪፐብሊካኑ ኮንግረስማን ካርል መንት ጠንሳሽነትና በኒውጀርሲው የፓርቲ አጋራቸው አሌክሳንደር ስሚዝ ድጋፍ በ1940 ህግ ሆኖ የወጣው በሰፊው “የስሚዝ-መንት አዋጅ” ተብሎ የሚጠራው ህግ ለአሜሪካ መንግስት መረጃ የማሰባሰብና የማሰራጨት መብት ሰጠ።
ለቲሻ ኪንግ የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ሃላፊ ናቸው። የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ የተቋቋመው “ነጻ መረጃን ያለምንም ቅድመ-ምርመራ ለተለያዩ የአለም ክፍሎች ለማድረስ ነው ይላሉ።
ነገር ግን የአገሪቱ መንግስት ይሄንን የመገናኛ መንገድ በአገር ውስጥ የህዝብ አስተያየትን ለመለወጥና ፕሮፓጋንዳ እንዳይነዛ በማሰብ በመረጃ ስርጭቱ ላይ “የስሚዝ-መንት” አዋጅ መጠበቂያ አብጅቷል ይላሉ።
የአሜሪካ መንግስት በዜጎቹ ላይ መረጃን እንደፈለገው እያሰራጨ ነጻ የመገኛኛ ብዙሃንን ስራም እንዳይጠቀልል ታስቦ በህግ ቪኦኤም ሆነ ሌሎች የማሰራጫ ጣቢያዎች በዩናይትድ ስቴይትስ እንዳይሰሙ ታግዷል።
የአሜሪካ ድምጽ በዩናይትድ ስቴይትስ ቢደመጥ በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር በምርጫ ወቅትና በሌሎች ጊዚያት የህዝብን ድጋፍ ለማግኘት እንዳሻው እንዳያዘውና እንዳይጠቀምበት፣ እና የመሳሰሉ ተቋማዊ ነጻነትን የሚንዱ ተግባሮች እንዳይኖሩ ለመከላከል ነው ገድብ ማብጀት ያስፈለገው ይላሉ የቪኦኤዋ ለቲሻ ኪንግ
የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮ ዛሬ በ42 ቋንቋዎች በአለም ዙሪያ መረጃን ይሰጣል። በእርግጥ በሬድዮና በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በአገር ውስጥ ባይሰራጭም፣ ህጉ ሲወጣ ኢንተርኔት ስላልነበረ አሜሪካዊያን ዛሬ በድረ-ገጽ መረጃውን ማግኘት ይችላሉ።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ምርጫ በቀረበ ቁጥር የአሜሪካ ድምጽ ሬድዮን ያፍናሉ በሚል በጋዜጠኛ መብት ተሟጋች ቡድኑ ሲፒጄና ሌሎች ድርጅቶች ይወቀሳል። አቶ መለስ ከ2002 የሀገር አቀፍ ምርጫ በፊት መንግስታቸው ቪኦኤን ለማፈን አቅም እየገነባ መሆኑንና ያን አቅም ገንብቶ ሲጨርስ “አፍኑ” የሚል ትእዛዝ እንደሚሰጡ በይፋ ተናግረዋል።
በቅርቡ በኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲም ቪኦኤ በኢትዮጵያ እንዳይሰማ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
“የአሜሪካ ድምጽ በአሜሪካ በህግ እንዳይተላለፍ ተከልክሏል….እኛም ከዚህ ከዩናይትድ ስቴይትስ ፖሊሲ አንድ ገጽ ወሰድንና ቪኦኤ በኢትዮጵያ አይሰማም አልን” ሲሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 29 ንኡስ አንቀጽ 2 እንዲህ ይላል
“ማንኛውም ሰው ያለማንም ጣልቃ-ገብነት ሃሳቡን የመግለጽ መብት አለው። ይህ ነጻነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሃገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሁፍ ወይንም በህትመት፡ በስነጥበብ መብት ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ ማንኛውንም አይነት ሃሳብ የመሰብሰብ፣ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል።”
በካሊፎርኒያ ስቴይት ዩኒቨርስቲ የህግ መምህር እና ጠበቃ የሆኑት አለማየሁ ገብረ-ማርያም የአቶ መለስ አባባል ህገ-መንግስቱ ጋር ይጋጫል ይላሉ።
“የአሜሪካ ድምጽ ወደ ኢትዮጵያ በሚገባው ህገ መንግስቱ ስለሚፈቅድ ነው” ይላሉ ፕሮፌሰር አለማየሁ።