“በቸልታ ከተውነው ያለአግባብ ይገለገሉበታል”- ሴናተር ቸክ ሹመር
የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት(ሴኔት)፣ በጦርነት ወቅት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት፣ የጦር ኃይልን በሰፊው እንዲጠቀም ሥልጣን የሚሰጠውን ሕግ ለመሻር እንቅስቃሴ ጀምሯል። በኹለቱም ፓርቲዎች ተወካዮች እየተደረገ ያለው ጥረት መነሻ ያደረገው፣ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት፣ ኮንግረሱ፥ የጦር ኃይልን ያለአግባብ መጠቀምን ሊያስቆም እና ሥልጣኑንም ሊያሳይ ይገባል፤ እያሉ ባለበት ወቅት ነው።
በኮንግረሱ ከወጡት ወሳኝ ሕጎች አንዱ፣ በጦርነት ወቅት ፕሬዚዳንቱ፣ የምክር ቤቱን ፈቃድ መጠየቅ ሳያስፈልገው የአገሪቱን የጦር ኃይል፣ ገደብ አልባ በኾነ ሥልጣን እንዲጠቀም የሚፈቅደው ሕግ ሲኾን፤ እአአ በ1991 በተካሔደው የባሕረ ሠላጤው ጦርነት እንዲሁም፣ እአአ በ2003 በተካሔደው የኢራቅ ጦርነት ወቅቶች፣ ፕሬዚዳንቱ የአገሪቱን ሠራዊት እንዳሻው ለመጠቀም አስችሎታል። አሁን ግን፣ በሕጉ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አንቀጾችን ማስቀረት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
በሴኔቱ አብላጫ ድምፅ የያዘው የዴሞክራቲክ ፓርቲው መሪ ሴናተር ቸክ ሹመር እንደተናገሩት፣ አሜሪካውያን በመካከለኛ ምሥራቅ በሚካሔደው ማለቂያ የሌለው ጦርነት ተሰላችተዋል፡፡ የኢራቅ ጦርነትን የመጀመሪያ ዓመታት የሚያስታውሱና በጉልምስና ዕድሜ የሚገኙ አሜሪካውያን በርካታ እንደኾኑ ያወሱት ሹመር፣ ፕሬዚዳንቶች፣ ወታደራዊ ኃይልን እንዳሻቸው እንዲጠቀሙ የሚፈቅደውን ሕግ በቸልታ ከተውነው፣ ለጥቀው የሚመጡት አስተዳደሮች ያለአግባብ ይገለገሉታል፤” ሲሉ የም/ቤቱን አባላት ሕጉን የመሻር እንቅስቃሴ አስፈላጊነት አስረድተዋል፡፡ የም/ቤት አባላቱ፣ “ቀኑ ያለፈበት ሕግ ነው፤” በሚል ለዓመታት ሕጉን ለመሻር ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል፡፡
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ሴናተር ዲክ ደሪንቢን፣ “የጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ኢራቅ ውስጥ አልተገኘም። የዚኽ ሕግ መሻር፣ አሜሪካ በጦርነት አስፈላጊነት የማታምን አገር ያደርጋታል ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ አሜሪካ ሕገ መንግሥታዊ አገር መኾኗን ነው የሚያሳየው፤” ብለዋል።
አንዳንድ የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካዮች ግን፣ የሕጉ መሻር፥ አገሪቱ ላይ አደጋ እያንዣበበ ባለበት ወቅት፣ ፕሬዝዳንቱ አፋጣኝ ርምጃ እንዳይወስድ እጁን ያስራል፤ በማለት ተቃውሟቸውን ይገልጻሉ፡፡
የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴው ሊንዚ ግራም፣ “አሜሪካኖች ኢራቅ ውስጥ እያገለገሉ ነው። ማንኛውንም ወታደራዊ ኃይል ተጠቅመን በኢራን በሚደገፉት ሻይቶች ከሚደርስባቸው ጥቃት መከላከል ግዴታችን ነው፤” በማለት ያስረዳሉ። ሕገ መንግሥቱ፣ “ፕሬዚዳንቱ የጦር ኃይሉ ዋና አዛዥ ነው፤” ስለሚል፣ ፕሬዚዳንቶች ያለኮንግረሱ ፈቃድ ወይም ኮንግረሱ ሳይገድባቸው ወታደራዊ ርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል።
ሕጉን መሻር ያስፈለገበት ምክንያት፣ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣኑን ያለ አግባብ እንዳይጠቀም ለመግራት እና በውጪ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች አደጋ በተደቀነባቸው ወቅት፣ ፕሬዚዳንቱ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡ ለማስቻል እንደኾነ ተገልጿል።
የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ እና የሴኔቱ የውጪ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበርሴናተር ባብ መንደዝ፣ “በቀጣናው፣ በእኛም ኾነ በአጋሮቻችን ላይ ኢራን የደቀነችውን አደጋ እረዳለኹ። ስለ እነርሱ ዓላማ እንደማናውቅ መኾን የለብንም። አስፈላጊ በኾነ ጊዜ፣ መቼ እና እንዴት መልስ መስጠት እንዳለብን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ሊኖረን ይገባል። የሕጉ መሻር፣ ከኢራን አንጻር የአሜሪካንን ጥቅም ከማስጠበቅ አያግደንም፤” ብለዋል።
ሕግ አውጪዎች፣ በዚህ ሳምንት በጉዳዩ ላይ ይከራከሩበታል፡፡ በሚያቀርቡት የመሟገቻ ነጥብ፣ የድምፅ ሰጪዎችን ትኩረት ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። ሕጉን ቀሪ የሚያደርገው የመሻሪያ አሳብ፣ ከሴኔቱ መቀመጫ የሚያስፈልገውን 60 ድምፅ እንደሚያገኝም ይጠበቃል።
በሌላ በኩል፣ አፍጋኒስታንን አስመልክቶ እአአ 2001 የወጣውን ሕግ ግን ሴኔቱ እንዲቀጥል ወስኗል። እንቅስቃሴው፣ የኹለቱንም ፓርቲዎች ድጋፍ ያገኘ ቢኾንም፣ ነቃፊዎችን አላጣም። ሪፐብሊካን ሴናተር ራንድ ፖል አንዱ ናቸው። “ኹለቱም ፓርቲዎች የሚሉት፣ በመስከረም 11 ቀን 2001 ለተፈጸመው ጥቃት የወጣው ሕግ፣ የጊዜም ኾነ የቦታ ወሰን የለውም ነው፤” ሲሉ የጠቀሱት ሴኔተሩ፣ “በኢራቅ ጦርነት ምክንያት የወጣውን ሕግ መሻር፣ ጦርነትን አያስቀርም፤ ሕይወትንም አያድንም፤” በማለት ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፡፡
ሕጉን የመሻር ሒደቱ፣ በሪፐብሊካኖች የበላይነት በተያዘው የተወካዮች ም/ቤትም ተቀባይነት ማግኘት ይኖርበታል። ከዓመታዊው የመከላከያ በጀት ጋራ ቀርቦ ክርክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።