በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

እንግሊዝ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅዷን እንደምትቀጥል አስታወቀች


እንግሊዝ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እቅዷን እንደምትቀጥል አስታወቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:08:32 0:00

የእንግሊዝ መንግሥት የመጀመሪያውን የስደተኞች ቡድን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ያደረገው ሙከራ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመታገዱ ቢከሽፍም፣ ከተለያዩ ዓለም የመጡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ ለመላክ ተጨማሪ በረራዎች እንደሚዘጋጁ መንግሥት ትላንት አስታውቋል።

ጥገኝነት ጠያቂዎችን ከእንግሊዝ ወደ ሩዋንዳ ለመውሰድ የሚደረገው በረራ እንዲከናወን ከሀገር ውስጥ ፍርድ ቤቶች ፈቃድ አግኝቶ የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ማክሰኞ ዕለት ሊያደርግ የነበረውን የመጀመሪያ በረራ የሰረዘው የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እቅዱ 'በስደተኞች ላይ ትክክለኛ እና ሊቀለበስ የማይችል አደጋ የደቀነ ነው' በማለቱ ነው።

የአውሮፖ ፍርድቤቱ ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ለመላክ የተዘጋጁት ስደተኞች ከሀገር እንዳይወጡ ቢከለክልም ግን የሀገር ውስጥ ሚኒስቴሯ ፕሪቲ ፓቴል በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር ወደፊት ለሚደረጉ በረራዎች የሚደረገው ዝግጅት ቀጥሏል ብለዋል።

"ከፍተኛው ፍርድቤት፣ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት እና ጠቅላይ ፍርድቤቱ በረራዎችን እንድናካሂድ መብት እንዳለን የወሰኑትን ውሳኔ እንቀበላለን። ሆኖም ስትራስበርግ የሚገኘው የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድቤት ዳኛ ባለቀ ሰዓት ጉዳዩ እስኪታይ ድረስ ስደተኞቹን የሚያስወጣው በረራ እንዲቆም አድርጓል።

አሁን ግልፅ ማድረግ የምፈልገው፣ የአውሮፓ ሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ፖሊሲው ወይም ስደተኞቹን የማዘዋወር ተግባሩ ህገወጥ ነው ብሎ አልወሰነም። ሆኖም በትላንቱ በረራ ላይ ተሳፍረው የነበሩ ሶስት ሰዎች እንዳይወጡ ነው የከለከለው። ይሄ ክልከላ ለተወሰነ ግዜ ሊቆይ ይችላል። ግን ወደ ሩዋንዳ የመላካቸውን ጉዳይ ጨርሶ የሚያቆመው አይደለም።"

ባሳለፍነው ሚያዚያ ወር በእንግሊዝ እና በሩዋንዳ መንግስታት መሀከል በተደረገው ስምምነት መሰረት የእንግሊዝ መንግስት በትናንሽ መርከቦች ተጭነው ወደ ሀገሩ የሚገቡ ስደተኞችን ወደ ሩዋንዳ የመመለስ እቅድ አለው። የሚያቀርቡት የጥገኝነት ጥያቄ በሩዋንዳ ታይቶ ተቀባይነት ካገኘ፣ እንደ ኢራቅ፣ አፍጋኒስታን እና ሶሪያ የመሳሰሉ ሀገራት የሚመጡ ስደተኞች ወደ እንግሊዝ በመመለስ ፋንታ በሩዋንዳ እንዲኖሩ ይፈቀድላቸዋል።

ሆኖም በስምምነቱ መሰረት ቀደም ብለው ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ሩዋንዳ የተወሰዱ ስደተኞች ለአሶስዬትድ ፕሬስ እንድተናገሩት በርካታ ችግሮች እየደርሱባቸው ነው።

ከነዚህ አንዱ የ22 አመቱ ወጣ ፒተር ናዮኒ እ.አ.አ በ2014 በደቡብ ሱዳን የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት ሸሽቶ ከሁለት ወንድሞቹ ጋር የተሰደደ ነው። ለህገወጥ አዘዋዋሪዎች ከፍተኛ ገንዘብ ቢከፍሉም፣ ሁለቱ ወንድሞቹ በመንገድ ላይ ሲገደሉ

እሱ ደግሞ በሊቢያ እስር ቤት ውስጥ ሰባት አመታትን አሳልፏል። ባለፈው አመት ማገባደኛ ላይ ደግሞ የተባበሩት መንግስታት የስደተኖች መርጃ ድርጅት ወደ ሩዋንዳ እንዲመጣ እንደተደረገ ይገልጻል።

"እኔ አሁን ማለት የምችለው ነገር የለም። እዚህ መኖር አልፈልግም። ወደፊት መሄድ ነው የምፈልገው። ወደ አውሮፓ ወይም ካናዳ - ብቻ እሄዳለሁ። እዚህ ግን አልቀመጥም።"

ፒተር አሁን ከሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ወደ 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘውና ወደ አውሮፓ ለመሄድ በሚያደርጉት ጥረት ለረጅም አመታት በሊቢያ ይኖሩ የነበሩ ስደተኞችን ለማስጠለል በተሰራው ጋሾራ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ይኖራል። ጋሾራ እንደ መተላለፊያ ጣቢያ ቢቆጠርም፣ እንደ ፒተር ያሉት ግን ምንም መሄጃ አይታያቸውም።

"ለእንግሊዝ መንግስት ማለት የምፈልገው የሰው ልጅ፣ የሰው ልጅ መሆኑን ነው። ስትፈልግ ሂድ ወይም እዚህ ሁን ልትለው አትችልም። ወይንም ይህን አርግ፣ ይህን አታርግ አይባልም። አይቻልም። ምክንያቱም እንግሊዝ ነው የሚሻለኝ ካለ እንግሊዝ ነው የሚሻለው። እንደሰውነታቸው ተቀባይነት ሊኖራቸው ይገባል እንጂ ወደ እዚህ ሊዘዋወሩ አይገባም። ወደ አፍሪካ ከመመለስ፣ እዛው እነሱ እስር ቤት ውስጥ መቆየት ይሻላል።"

ሩዋንዳ በዓለም ላይ በርካታ ህዝብ በትንሽ ቦታ ተጣቦ የሚኖርባት ሀገር ናት። እ.አ.አ በ1994 ዓ.ም ከተካሄደው የዘር ጭፍጨፋ በኃላ ሀገሪቱ በልማት ላይ ብታተኩርም አሁንም ደሃ ከሚባሉ ያላደጉ ሀገራት መሀክል አንዷ ናት።

የሩዋንዳ ባለስልጣናት ሀገራቸው ስደተኞችን በመቀበል የሚያኮራ ታሪክ እንዳላት ቢናገሩም፣ በእንግሊዝ የተሻለ ህይወት ለማግኘት ተስፋ ያደርጉ ለነበሩት ስደተኞች ግን በሩዋንዳ ህልማቸውን ሊያሳካላቸው የሚችለው እድል አናሳ ነው።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ቀደም ሲል ከተቋሙ ጋር በተደረገ ስምምነት ወደ ሩዋንዳ ተልከው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁን ወደ ሶስተኛ ሀገር ተልከዋል። ሆኖም ከእንግሊዝ ጋር በተደረገው ስምምነት ወደ ሩዋንዳ የሚላኩ ስድተኞች ግን ለጥገኝነት ማመልከት የሚችሉት ሩዋንዳ ውስጥ ነው።

የእንግሊዝ መንግስት እንደሚለው የሰዎችን ህይወት አደጋ ላይ በመጣል ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከሚያዘዋውሩ ወንጀላኛ ቡድኖች ለመታደግ ይሄ መንገድ ትክክለኛው አማራጭ ነው።

"ይሄ መንግስት ትክክለኛውን መንገድ ለማድረግ አይፈራም። ባለቀ ደቂቃ ሊመጡ በሚችሉ የህግ ፈተናዎች አንሸነፍም። ወይም ስደተኞችን የማዘዋወሩን ስራ አመፀኞች እንዲያደናቅፉት አንፈቅድም። አፀያፊ ስራ የሚሰሩ የተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች፣ ሰዎችን እንደ ካርጎ እቃ የሚያዘዋውሩ ክፉ ሰዎችን ቁጭ ብለን እንደልባቸው ሲሆኑ አናይም። ድንበራችንን ለመቆጣጠር መብት የላችሁም መባልን አንቀበልም። የዚህን ሀገር ደህንነት ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ እናደርጋለን፣ ለረጅም ግዜ በኖረው ባህላችን መሰረትም የእውነት ችግር ውስጥ ያሉትን መርዳት እንቀጥላለን።"

የአውሮፖ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የእንግሊዝ ፍርድቤቶች ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የሚወስደው በረራ እንዲከናወን የሰጡትን ፈቃድ አልሻረም። ሆኖም የእንግሊዝ ፍርድ ቤት በረራው እንዲከናወን ሲፈቅድ በእያንዳንዱ ተሳፋሪ ስደተኛ ይዞታ ላይ የሰጠው ብይን ባለመኖሩ የአውሮፓ ፍርድ ቤት ለእግድ ተጠቅሞበታል።

የእንግሊዝ መንግስት እቅድ ተግባራዊነት፣ በሀገሩ ፍርድ ቤቶች ለመታየት በሐምሌ መጨረሻ ፈቃድ የተያዘ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ጠበቃ የሆኑትና በአውሮፓው ፍርድ ቤት መከራከሪያቸውን ያቀረቡት ጆፈሪ ራበርትሰን፣ ስደተኞች የጥገኝነት ጥያቄያቸውን በሩዋንዳ እንዲያቀርቡ መደረጉ፣ መንግስት ከመጡበት ሀገር ጋር ግንኙነት ካለው፣ ሸሽተው ወደመጡበት ሀገር እንዲመለሱ ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልፀዋል።

"የሩዋንዳ ዳኛ አንድ ስደተኛ የእውነተኛ ጥገኛ ጠያቂ ነው ብሎ ቢወስን፣ እዛው ሩዋንዳ እንዲቀር ነው የሚደረገው። ወደ እንግሊዝ የመመለስ መብት የላቸውም። ፍርድ ቤቱ ከሚያያቸው ጉዳዮች አንዱም ይሄ ይመስለኛል ምክንያቱም፣ ሩዋንዳ ውስጥ ዝም ብለው እንዲቀሩ ከተደረገ መንግስት 'ከኢራን የመጣ የመንግስት ተቃዋሚ ወደ ኢራን ከተመለሰ ልገደል እችላለሁ ብሎ ይፈራል' ይላል። የሩዋንዳ መንግስት ደግሞ ከኢራን ጋር የቀረበ ግንኙነት ስላለው ያ ሊፈጠር ይችላል።"

የስደተኞች ጉዳይ የሚከታተሉ ቡድኖችም ወደ ሩዋንዳ መላኩ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወደ እንግሊዝ ለመሄድ አስቸጋሪ ጉዞ የሚያደርጉትን ጉዞ ያስቀራል የሚለው እቅድ የማይሳካ ነው ይላሉ። ለምሳሌ ማክሰኞ እለት ድርስ እርጉዞችንን እና ህፃናትን ጨምሮ 440 ሰዎችን የያዘ ጀልባ በደቡብ እንግሊዝ ወደ ላይ አርፏል። በበርሚንግሃም ዩንቨርስቲ የስደተኛ ጉዳዮች ባለሙያ የሆኑት ናንዶ ሲጎና ይህ የሩዋንዳ እቅድ ስደተኞቹ የሚጠቀሙበትን መንገድ ሊቀይር ይችላል ይላሉ።

"ወደ ሩዋንዳ የማዛወሩ እቅድ ስደተኞች በእንግሊዝ ካናል ውስጥ ለማለፍ የሚጠቀሙበትን መንገድ እንዲቀይሩ ያደርጋቸዋል። በዚህ ፖሊሲ ውስጥ የተካተቱት በተለይ ያላገቡ ወንዶች ወደ ሩዋንዳ የመመለስ ስጋት ስለሚኖርባቸው የስደተኛ ዝውውር ስልቱን ይቀይሩታል። ከዚህ ቀደም እንዳየነው የፖሊሲ ለውጦች የስደት መንገዳቸውን እንዲቀይሩ ያደርጋል። እናም ደግሞ በጅልባው የሚሳፈሩት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ልጆች፣ ቤተሰቦች እና ሴቶች ይሆናሉ። ምክንያቱም እነሱ ወደ ሩዋንዳ በመመለሱ እቅድ ውስጥ ኢላማ የተደረጉ አይደሉም ተብሎ ስለሚታሰብ።"

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም የእንግሊዝ እቅድ፣ ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ተከትሎ ለስደተኞች የተሰጠውን የጥበቃ ከለላ የሚጋፋ መሆኑን በመግለፅ ይከራከራሉ። ሀሳቡ በተግባር መዋል የማይችል፣ ኢ-ሰብዓዊ እና ለገንዘብ ብክነት የሚዳርግ ነውም ይላሉ። እንግሊዝ ከሩዋንዳ ጋር ለገባችው ስምምነት 120 ሚሊየን ፓውንድ ወይም 150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ቅድመ ክፍያ ፈፅማለች።

XS
SM
MD
LG