በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ክልል በተስፋፋው ካላዛር በሽታ ስድስት ሰዎች ሞቱ


በደቡብ ክልል በተስፋፋው ካላዛር በሽታ ስድስት ሰዎች ሞቱ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:37 0:00

· በክልሉ ከሦስት በላይ ዞኖች መዛመቱ ተገልጿል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ በተስፋፋው ካላዛር በሽታ፣ በአንድ ወር ውስጥ ስድስት ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።

የአካባቢው የጤና ተቋማት ሓላፊዎች እና የሕክምና ባለሞያዎች፣ በአካባቢው ከሰባት ወራት በፊት የተከሠተው በሽታ በመስፋፋት ላይ መኾኑን ተናግረዋል። ከደቡብ ኦሞ ዞን ብቻ፣ በበሽታው ከተያዙት 150 ሕሙማን 17ቱ በስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ መሞታቸውን፣ የዞኑ ጤና መምሪያ አስታውቋል። በሽታው፥ በኮንሶ፣ በጋሞ እና በጎፋ ዞኖችም መዛመቱን የሆስፒታል ምንጮች አረጋግጠዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን የጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ አብርሃም አታ፣ የወረርሽኙ ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአካባቢው ላይ እየተባባሰ እንደመጣ አስታውቀዋል።

አቶ አብርሃም “በአሁኑ ሰዓት ሕሙማኑ ከ150 በላይ ደርሰዋል። ወደ ሆስፒታል መጥተው ከነበሩት የ17 ሰዎች ሞት ተመዝግቧል። ቀደም ሲል የበሽታው መከሠት ሪፖርት ያልተደረገባቸው ወረዳዎች፣ አሁን እየተደረገባቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ ከ150 ሕሙማን ውስጥ ከ100 በላይ የሚኾኑቱ፣ ሳላማጎ ከሚባል ወረዳ እየመጡ ነው” ያሉ ሲሆን በሌሎች ሰባት ወረዳዎችም፣ ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል። “ከጂንካ ሆስፒታል አልጋዎች፣ 25 በመቶው በበሽታው ታማሚዎች ነው የተያዘው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታሉ ከ24 በላይ ታማሚዎች አሉ።”ብለዋል።

የጂንካ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋየሱሰ ተፈራ፣ ባለፈው ወር፣ በወረርሽኙ የታመሙ ሰዎች በሆስፒታላቸው ተኝተው እየታከሙ መኾኑን ጠቁመው፣ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ለቪኦኤ በስልክ ተናግረው ነበረ።

የዞኑ የጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ አብርሃም፣ በአንድ ወር ልዩነት በበሽታው የተያዙ እና የሞቱ ሰዎች መጨመሩን ጠቅሰው፣ ኹኔታው ከዐቅም በላይ እንደኾነ አስታውቀዋል፡፡

አቶ አብርሃም ፤ “የበሽታውን መስፋፋት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር አልተቻለም። በየጊዜው ታማሚ እየገባ ነው ያለው። ከዚያ ውጭ ሆስፒታሉ የተሟላ ሕክምና ለመስጠት በሚያስችለው ቁመና ላይ አይደለም ያለው። በበሽታው ላይ በቂ የሠለጠነ የሰው ኀይል አለመኖር አንዱ ችግር ነው።” ካሉ በኋላ “17 ሰዎች ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ ነው የሞቱት። ከዚያ ውጭ በሆስፒታሉ ውስጥ ከፍተኛ የደም እጥረት አለ፡፡ እንግዲህ ታማሚዎች በትንሹ አምስት ዩኒት ደም ይወስዳሉ። ከዚኽ የተነሳ ታማሚው፣ በጣም የተወሳሰበ ኹኔታ ውስጥ ኾኖ ሲመጣ፣ ለማዳን በጣም እየተቸገርን ያለንበት ኹኔታ ነው ያለው።” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ወረርሽኙን አስመልክቶ ቪኦኤ ያነጋገራቸው የደቡብ ኦሞ ዞን ነዋሪዎች፣ በሽታው እየተስፋፋ እና ጉዳት በማድረስ ላይ እንደኾነ መናገራቸው ይታወሳል። አቶ አብርሃም፣ በአሁኑ ወቅት በሽታው ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመዛመት ላይ መኾኑን ይናገራሉ።

በአርባ ምንጭ ሆስፒታል፣ የውስጥ ደዌ ሐኪም ዶክተር ዐዲሱ ተስፋዬ፣ በካላዛር ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎች፣ በሆስፒታላቸው ተኝተው በመታከም ላይ መኾናቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ካላዛር የምንለው በሽታ፣ የሰውን አካላትን የሚያጠቃ የቆዳ እና የጣፊያ በሽታ ነው። ወደ አርባ ምንጭ ሆስፒታል ከአካባቢው ማለትም ከኮንሶ እና ከጂንካ ኬዞች ይመጣሉ። በተለያየ ወቅት

ተለዋዋጭ የሕመምተኛ ቁጥር ይኖራል። አሁን በዋርድ ወስጥ ሦስት ታካሚዎች አሉ። በቅርብ ጊዜ በሕይወት ያለፉ የሉም፤ ነገር ግን በበሽታውም ኾነ በመድኃኒቱ የጎንዮሽ ጉዳት፣ ሞት አጋጥሞን ያውቃል።

ወረርሽኝ ተብሎ በሚነገር ደረጃ ላይ ባይደርስም፣ በካላዛር የተያዙ ሰዎች በኮንሶ ዞንም እንዳሉ፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ ደይካንቶ ኡርማሌ ገልጸዋል።

“የቆዳ እና የሆድ ካላዛር አለ። እኛ ጋራ ያለው የሆድ ልሽማኒያ ነው። አባሮባ በሚባል አካባቢ እና በኬና ወረዳ በቦረና ድንበር ይገኛል፤ ወደ ካራት ከተማ አከባቢም አለ። አልተደረሰበትም እንጂ ታማሚው ከበዛ እና ከአረጋገጡ እንቀበላለን። አሁን ላይ፣ እንደ ኮንሶ ዞን ጤና መምሪያ መረጃ እኔ የምለው፣ በወረርሽኝ መልክ ተከሥቷል፤ የሚል ሪፖርት አልደረሰንም።

የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ፣ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። ይኹን እንጂ፣ ኤምኤፍኤስ ቤልጂየም የተሰኘ መንግሥታዊ ያልኾነ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ክትትል እያደረጉ መኾናቸውን፣ የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ሓላፊ አቶ አብርሃም ገልጸዋል። የሐኪሞች፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና የመድኃኒት እጥረት እንዲሁም የዐቅም ማነስ መኖሩንም ጠቁመዋል።

ገዳቱ ከፍተኛ መኾኑ የተገለጠው ይኸው ካላዛር የተባለው ወረርሽኝ፣ የአሸዋ ትንኝ በተሰኘች ቢንቢ የተነሣ፣ ከጉበት እና ከጣፊያ ጋራ የተገናኘ ደም የሚያስቀምጥ እና የሚያስመልጥ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ በሽታ እንደኾነ የሕክምና ባለሞያዎች አስረድተዋል።

ዝርዝሩን ከተያያዘው ዘገባ ያገኛሉ።

XS
SM
MD
LG