በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ ክልል አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ 51 ሰዎችን ገደለ


በደቡብ ክልል አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች የኮሌራ ወረርሽኝ 51 ሰዎችን ገደለ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:47 0:00

በደቡብ ክልል በአማሮ ልዩ ወረዳ በተከሠተ የኮሌራ ወረርሽኝ፣ ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ፣ አራት ሰዎች መሞታቸውን፣ የወረዳው አስተዳደር ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በቡርጂ ልዩ ወረዳ ደግሞ፣ ሦስት ሰዎች በወረርሽኙ ሕይወታቸው ማለፉን፣ የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት፣ ቀጣናው በወረርሽኙ መበከሉንና አስጊ መኾኑን ተናግረዋል።

የአማሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት፣ የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዋና ሥራ ሒደት የማኅበረሰብ ተግባቦት እና የጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ካሌብ፣ በስልክ ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለጹት፣ በወረዳው ውስጥ በተከሠተው የኮሌራ ወረርሽኝ፣ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል።

በወረርሽኙ፣ ሦስት ሰዎች የሞቱበት ዬሮ ቀበሌ ውስጥ፣ ሌሎች ሦስት ሰዎች በጠና መታመማቸውን፣ አቶ አክሊሉ ተናግረዋል።

ከሟቾቹ ውስጥ አንደኛው፣ ከሞያሌ ተነሥተው በቡርጂ አድርገው ወደ አማሮ ኬሌ በመጓዝ ላይ የነበሩ የወረዳው ነዋሪ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ አክሊሉ፣ በቡርጂ ጤና ጣቢያ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በዚያው ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።

በወረዳው ስለ ወረርሽኙ ተዛማችነት የተጠየቁት፣ የቡርጂ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ትምህርቴ ኃይሉ፣ በወረዳው ወረርሽኙ መከሠቱን አረጋግጠው፣ ሰዎችም መሞታቸውን አመልክተዋል።

ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋላና ወረዳ ኮምቦልቻ ቀበሌ ወደ አማሮ ኬሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የገቡ ሁለት ሰዎች፣ ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ድነው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን፣ የአማሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት የበሽታ መከላከል እና ጤና ማጎልበት ዋና ሥራ ሒደት የማኅበረሰብ ተግባቦት እና የጤና ኤክስቴንሽን አስተባባሪ አቶ አክሊሉ ገልጸዋል። በየአካባቢዎቹ፣ የኮሌራ ወረርሽኝ፣ “በፍጥነት እየተዛመተ ነው፤” ሲሉም ጠቁመዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(OCHA)፣ ሰሞኑን በአወጣው ሪፖርት፣ እ.አ.አ. ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር አንሥቶ፣ የደቡብ ክልልን ጨምሮ በሌሎችም ክልሎች በተከሠተው ወረርሽኝ፣ ከአራት ሺሕ በላይ ሰዎች መያዛቸውንና 71 ሰዎች መሞታቸውን አስታውቋል::

የልዩ ወረዳዎቹ የጤና ጥበቃ ጽ/ቤት የባለሞያዎች ቡድን፣ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ከተላከው ቡድን ጋራ፣ የሕክምና መድኃኒት እና ቁሳቁሶችን ይዘው፣ ወረርሽኙ ወደተከሠተባቸው አካባቢዎች መንቀሳቀሳቸውን ቢሮው አመልክቷል።

ኅብረተሰቡ ንጽሕናውን በመጠበቅ፣ ምግብ አብስለው ብቻ በመብላት እና የሚጠጡትንም ውኃ በማፍላት፣ በሽታውን እንዲከላከል አሳስበዋል።

XS
SM
MD
LG