በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በደቡብ አፍሪካ የወንጀል መበራከትን ተከትሎ የፖሊስ አመራሩ እንዲለወጥ ተጠየቀ


በደቡብ አፍሪካ የወንጀል መበራከትን ተከትሎ የፖሊስ አመራሩ እንዲለወጥ ተጠየቀ
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:32 0:00

በደቡብ አፍሪካ የአመጽ ወንጀሎች መበራከታቸውን ተከትሎ በገና በዓል ተጨማሪ 10ሺ አዳዲስ ፖሊሶችን በጎዳና ላይ እንደሚያሰማራ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በደቡብ አፍሪካ ግድያ በ14 በመቶ፣ የመኪና ስርቆት 24 በመቶ፣ እንዲሁም አፈናዎች በእጥፍ መጨመራቸው ተነግሯል፡፡

ከሀምሌ እስከ መስከረም ባሉት የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 1ሺ የሚጠጉ ሴቶችን ጨምሮ፣ 7ሺ ሰዎች መገደላቸውን እና 10ሺ ሴቶች መደፈራቸውን ፖሊስ አመልክቷል፡፡

ይህ አስጨናቂ ዜና የተሰማው ጾታዊ ጥቃቶችን ለመቃወም ከዛሬ ጀምሮ ለ16 ቀናት የሚካሄደው የመብት ተሟጋቾች ዘመቻ ከመጀመሩ በፊት ነው፡፡

ከሀምሌ እስከ መስከረም ባሉት የሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ያለውን የወንጀል መጠን ያስታወቁት የፖሊስ ሚኒስትሩ ቤኪ ሴል የወንጀል አሃዙ በደቡብ አፍሪካ ሁከትና ጥቃት በአሳሳቢ መጠን መጨመሩን ያሳያል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም "የ10ሺ ተጨማሪ ፖሊሶች መመደብ በገና በዓልና ከዚያም ጊዜ በኋላ ላሉት ጊዜያት ለውጥ የሚያመጣ" መሆኑን በመግለጽ ለዜጎቻቸው ተስፋ ሰጥተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከደህንነት ጥናት ተቋም የወንጀል ተንታኝ የሆኑት ጋርትዝ ኒውማን ጥርጣሬ አላቸው።

ከአስር ዓመታት በፊት አንስቶ ከፍ እያለ የመጣው የግድያ ወንጀል እየጨመረ ሲሆን የሚጨምርበትም መጠን አስከፊ እየሆነ መምጣቱን ኒውማን ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ወንጀልን የመከላከል ጥረት እየቀነሰ መምጣቱን በመግለጽ “የመንግሥትን ትልቅ አቅም ማንቀሳቀስ አልቻለም።” ብለዋል፡፡

“ይህንን ስንል በዓመት ወደ 8.8 ቢሊዮን ዶላር ወደ ወይም 140 እስከ 150 ቢሊዮን ራንድ የሚደርሰውን ለወንጀል ፍትህ የተመደበውን በጀት ነው የምናወራው። ወንጀለኞችን ለፍትህ ለማቅረብ ወደ 180ሺ የሚጠጉ ሠራተኞችን በሚገባ መጠቀም አልቻሉም።” ሲሉም ኒውማን አስረድተዋል፡፡

ኒውማን "እኤአ በ2012 አንስቶ እስካለፈው ዓመት ድረስ የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ለግድያ መፍትሄ የመፈለግ አቅም በ50 ከመቶ ወርዷል" ይላሉ።

መንግሥት ለውጥ ለማምጣት እንዲችል ቢያንስ በራሱ በመንግስት ከተደገፉ አራት አጣሪ ኮሚሽኖችና ባለፉት ዓመታት የነበሩትን የፖሊስ አሰራሮች ያጠኑትን የባለሙያዎች ቡድን አስተያየት መመልከት አለበት ሲሉም ኒውማን አሳስበዋል።

“ከፍተኛውን የደቡብ አፍሪካን ፖሊስ አገልግሎት አስተዳደር እርከን ሙሉ ለሙሉ እንደገና ከማደስ መጀመር አለብን ፣ ምክንያቱም ችግሩ የሚጀምረው ከዚህ ነው። የአስተዳደር መዋቅሩ ከራሱ ጋር ጦርነት ውስጥ ነው።” ይላሉ ኒውማን፡፡

"1ሺ ሴቶች አንድ ድምጽ" የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት መስራች ቲና ቲያርድ፣ የወንጀል ሥርዓቱን ለማሻሻል የሚቻልበት ብዙ መንገድ በመኖሩ ይስማማሉ፡፡

ጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃትን ለመቃወም ዓርብ በጀመረውና የ16 ቀናት በሚፈጀው ንቅናቄ ላይ ለመሳተፍም መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ለሴቶች “እኔም እንዲሁ” የተሰኘውን የውይይት ክበብም አዘጋጅተዋል፡፡

“በአገር አቀፍ ደረጃ ግን ለፕሬዚዳንቱ የሚላኩ ፖስት ካርዶች እያዘጋጀን ነው፡፡” ያሉት ቲያርድ “በፖስት ካርዶቹ ላይ መፍሄዎችን እንሰጣቸዋለን፣ በሴትነታችን ከኛ ከሴቶች የፈለቀ መፍትሄ፡፡” ብለዋል፡፡

ለምሳሌ አንዳንዶቹ መፍትሄዎች ምንድናቸው? የሚለውን ጥያቄ ቲያርድ ሲመልሱ “በፖሊስ እና ማህበረሰብ አቀፍ በሆኑ ድርጅቶች መካከል ያለውን ግንኙነታችንን ማጠናከር፡፡ ፖሊስ በሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች ብቻ ሳይሆን በፖሊስ ጣቢያዎችም በኩል ድጋፍ ሊሰጡ የሚችሉ ብዙ ተጨማሪ ድጋፍ ሰጭዎችን ማሰልጠን፡፡” በማለት ዘርዝረዋል፡፡

“ያ ሲሆን ሴቶች ፖሊስ ወደ ሚያስፈልጋቸው አገልግሎት ሰጭዎች ወደ ፍርድ ቤቶች፣ ወደ ክሊኒኮች ሲሄዱ፣ ሊታጀቡ ይችላሉ” ብለዋል ቲያርድ፡፡

ቲያርድ በገጠር የጾታ ጥቃት የሚደርስባቸው ሴቶች ደህንነታቸው ወደ ተጠበቀበት ሠፍራ እስኪደርሱ ድረስ በሚሰጠው አገልግሎት ዙሪያም ሥልጠና እየሰጡ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

XS
SM
MD
LG