በአፍሪካ ቀንድ ባለፉት 60 ዓመታት ውስጥ ከታዩ ሁሉ የከፋ የተባለው ድርቅና ረሃብ ወደ 13 ሚሊዮን ህዝብን ለአስቸኳይ እርዳታ ባጋለጠበት ወቅት፤ በድርቁ ክፉኛ በተጎዳችው ሶማሊያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚያቀርበውን እርዳታ የሚያስተባብሩት ማርክ ቦደን” ለቪኦኤ ሲናገሩ፤ የአለም አቀፍ እርዳታ ለውጥ ማምጣቱን አስምረውበታል።
“የከፋው የረሃብና ቸነፈሩን ጊዜ ለመከላከል ችለናል። በሃምሌ ወር በሶማሊያ ረሃብና ቸነፈር ተስፋፍቷል ብለን ስናውጅ ወደ 8 የሚሆኑ ክፍለ-ሃግሮች ይራባሉ ብለን አስበን ነበር። ከጥር ወር በፊት ባለው ጊዜ በረሃብና ቸነፈር ሞት ተጋርጦባቸው የነበሩትን ሰዎች ቁጥር ከ750ሽህ ወደ 250ሽህ ዝቅ ማድረግ ችለናል” ብለዋል ቦደን።
የህጻናትና የእናቶች ሞትም በሶስቱ የረሃብና ቸነፈር ቀጠናዎች በእጅጉ መቀነሱን ነው ባለስልጣኑ የሚናገሩት። ያም ሆኖ ሁኔታው አሁንም አስጊና ሊያገረሽ የሚችል እንደሆነ ቦደን ያሳስባሉ። አሁንም 4 ሚሊዮን ሰዎች በሶማሊያ ውስጥ አስቸኳይ እርዳታ ይሻሉ። እነዚህ ሰዎች የምግብ እርዳታና የኑሮ ማቋቋሚያ ካላገኙ ተመልሰው ወደ ረሃብ ሊወድቁ እንደሚችሉ ቦውደን ይናገራሉ።
የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪው ቦውደን በዩናይትድ ስቴይትስና አውሮፓ፤ በቀጣይነት ሶማሊያዊያንን መልሶ ለማቋቋም የታሰበ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ በጀትን ለማሟላት፤ መንግስታትን በመማጸን ላይ ናቸው።
በድርቁ በተጠቁ የሶማሊያ አካባቢዎች፣ በደቡብና ምስራቅ ኢትዮጵያ እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ኬንያ በመስከረምና ጥቅምት አጭር የዝናብ ወቅት፤ በቂ ዝናብ ተገኝቷል። የተገኘውን ዝናብ ተጠቅመው ገበሬዎች ሰብሎች እንዲዘሩ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየጣረ ይገኛል።
ገበሬዎች ምርታቸውን ወደ ጎተራ፤ ወይም መሬት እንደሰጠው ወደ ኬሻ እስኪያስገቡ ድረስ ግን፤ አሁንም በድርቁ የተጠቁ አካባቢዎች አስቸኳይ እርዳታ ያሻቸዋል። ወትሮውንም በደህናው ጊዜ የጥቅምት ወር ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ፤ የድርቅ ወቅት በመሆኑ፤ ከአሁኑ ወቅታዊ ምርት ጋር ቀጣዩ የዝናብ ወቅትም ወሳኝ እንደሚሆን የእርዳታ ሰራተኞቹ ያብራራሉ።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት ከአገር በቀል ድርጅቶችና መንግስታት ጋር በቅንጅት የሚያደርጓቸው እንቅስቃሲዎች በሶማሊያ ላለፉት 20 ዓመታት የዘለቀው ጦርነት ሲያጨናግፈው ይታያል።
በድርቁ ከተጎዱ ሰዎች መካከል ወደ 60ከመቶ የሚሆኑት የሚኖሩት በእስልምና አማጺው ቡድን አልሸባብ ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎች ነው። በዚህ የተነሳ እርዳታ ላማዳረስ የሚያስችሉ መንገዶችና የፖለቲካ ፈቃደኝነቶች ፈታኝ ችግሮች ነበሩ።
የምእራባዊያን መንግስት በጽኑ የሚቃወመው አልሸባብ፤ እርዳታ በችግር ላይ የሚገኙ ሶማሊያዊያንን እንዳይደርስ በተደጋጋሚ ያግዳል። በተለይ ሞቃዲሹ የሚገኘውን የሽግግር መንግስት የሚያግዘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአሜሪካ እርዳታ በሸባብ በተያዙት ማእከላዊና ደቡባዊ ሶማሊያ እንዲደርሱ አማጺያኑ አይፈልጉም።
በዚህ እክል የተነሳ የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል በዚህ ሳምንት (ባለፈው ሳምንት) ለ1.1 ሚሊዮን ሶማሊያዊያን ያቀርብ የነበረውን እርዳታ አቋርጧል። ይሄም ሊሆን የቻለው የአልሸባብ ባለስልጣናት ድርጅቱ በማእከላዊና ደቡብ ሶማሊያ እርዳታ እንዳያከፈፍል በመከልከላቸው እንደሆነ አስታውቋል።
ሁኔታው የእርዳታ አሰጣጡን ክፉኛ እንዳይጎዳው ተሰግቷል። የተባበሩት መንትስታት ድርጅት የሶማሊያ እርዳታ አስተባባሪ ማርክ ቦደን የቀይ መስቀል ውሳኔ ጊዚያዊ እንደሚሆን ይናገራሉ።
“ሳነጋግራቸው ሁኔታው ጊዚያዊ እንደሚሆን ተስፋቸውን ገልጸውልኛል። ሆኖም የማህበረሰቡን የምግብ ችግር ለመቅረፍ የሚያስችሉን ሌሎች መንገዶች አሉ፤ ዋናው ነገር እርዳታውን ለማድረስ የሚያስችሉ መንገዶችን ማፈላለጉ ነው።”
ከነዚህ መንገዶች አንዱ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ አጋሮችን ማፈላለግ ነው።
“አብረናቸው የምንሰራው ከ200-300 የሚሆኑ አገር በቀል አጋሮች አሉን” ይላሉ ቦደን። “ሰፊ የሆነ የመረጃ መቀባበያና ሁኔታ የመገምገሚያ መንገዶች አሉን። ከነዚህ አጋሮቻችን ጋር ሆነን ክፍተቶቹ በየትኞቹ አካባቢዎች እንዳሉና እንዴት እርዳታ ማድረስ እንደሚቻል እንመካከራለን።”
እርዳታውን ወደ ሶማሊያ ለማድረስ የተደቀኑ የደህንነት ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት በአልሸባብ ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪዎች፣ የጎረቤት ኬንያና ኢትዮጵያ ወታደሮች የጀመሩትን ጥቃት ተንተርሶ፤ እርዳታ ለማከፋፈል የሚያስችል ጸጥታ ይኖር ይሆን? ማርክ ቦደን
“በእውነቱ ይሄንን አላውቅም። የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱን በአንድ በኩል ወይ በሌላ ይለውጠዋል ብየ መናገር አልችልም። ዋናው ተስፋችን ግጭቱ አቢይ የምግብ እርዳታ ማሰራጫ መንገዶችን አይዘጋም የሚል ነው። ግጭቶቹም ተጨማሪ ሰዎችን ለስደት እንዳያጋልጡ በሁሉም ወገኖች ጥረት እንዲደረግ ጥሪ እናስተላልፋለን።”
ሚስተር ቦድን በዚህ ሳምንት በሰሜን አሜሪካና አውሮፓ በሶማሊያ ያለውን የሰብዓዊ ቀውስ ለመሪዎች ለማሳወቅና፤ ተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና የመልሶ ማቋቋሚያ ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ ናቸው። በሶማሊያ ያለው ድርቅና ረሃብ እስከ መጨው ነሃሴ ወር ሊቀጥል እንደሚችልም አሳስበዋል።