በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን ለማሳደግ እየሠራች መሆኑን አስታወቀች


ሶማሊያ የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ፍሰትን ለማሳደግ እየሠራች መሆኑን አስታወቀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:56 0:00

ሶማሊያ ለመጀመሪያ ግዜ በሀገሯ ባካሄደችው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለችው ለውጥ ተጨማሪ መዋዕለ ንዋይ ወደ ሀገሯ እንዲፈስ የሚያግዝ መሆኑ ተመልክቷል። ለሁለት ቀናት በተደረገው ጉባኤም የመንግሥት እና ዓለም አቀፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሶማሊያ የፌዴራል መንግሥት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች እና ሌሎች የሶማሊያ ኅብረተብ ክፍሎች ሰኞ እና ማክሰኞ በዋና ከተማው ተሰባስበው በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ግዜ የተካሄደውን ዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ጉባኤ ተካፍለዋል። ጉባኤው ሶማሊያ በፖለቲካው እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እያስመዘገበች ያለውን እድገት ዓለም የሚያደንቅበት እድል የፈጠረ መሆኑም ተገልጿል።

ሁለት ቀን በቆየው ጉባኤ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃመድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሶማሊያ የሚያደርገውን ድጋፍ አድንቀዋል።

"ዓለም ሶማሊያን ላለፉት ሦስት አስርት አመታት በሰብዓዊ እርዳታ ሲደግፋት ቆይቷል። ዛሬ እዚህ ፊታችሁ ቆሜ ለዓለም ህዝብ የማቀርበው ጥሪ፣ ሶማሊያ ጽንፈኝነትን ጨምሮ ለብዙ ችግሮች ምክንያት ከሆነው ድህነት ነፃ እንድትወጣ መዋዕለ-ንዋይ በማፍሰስ እንድትረዷት ነው"

ፕሬዚዳንቱ አክለው ሶማሊያ ካለችበት ድህነት ለመውጣት ኢኮኖሚዋን ማሳደግ ቁልፍ መሰረት መሆኑን ተናግረዋል።

"የበለፀገች ሀገር እንዲኖረን የሶማሊያ ህዝብ እና የሶማሊያ መንግሥት ዋና አላማ ጥሩ ኢኮኖሚ እንዲኖረን ማድረግ እና የድህነት መጠኑን መቀነስ ነው። ለዚህ የሶማሊያ ኢኮኖሚ እድገት ደግሞ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይ ምን ያክል አስፈላጊ መሆኑን ከፍተኛ አፅንኦት መስጠት እፈልጋለሁ። የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይ ሥራ ይፈጥራል፣ ወደ ውጭ የሚላክ ምርት ይጨምራል እናም ለሀገሪቱ የሚገባውን ገቢ እና የታክስ ጣሪያ እያሰፋው ይሄዳል።"

ፕሬዚዳንት ሞሃመድ፣ ሶማሊያ ለዓመታት ከኖረችበት ግጭት አገግማ ሀገሪቱን እንደገና ለመገንባት ጥረት እያደረገች ባለችበት ወቅት መንግስት ህገመንግሥታዊ አስተዳደር፣ መረጋጋት እና ዲሞክራሲን በማስፈን የውጭ ቀጥታ መዋዕለ-ንዋይን የሚስብ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረትም አብራርተዋል።

'የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን የዘርፍ መዋዕለ ንዋይን መክፈት' በሚል መሪ ቃል የተካሄደውን ጉባኤ ያዘጋጀው የፌዴራል የፕላን፣ ኢንቨስትመንት እና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከግሉ ዘርፍ እና የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ሲሆን በሶማሊያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ድጋፍ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ምክትል ልዩ ተወካይ እና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ የሆኑት አደም አብደልሙላ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢንቨስትመንት ጉባዔው በሶማሊያ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.አ.አ የ2030 ዘላቂ ልማት ግቦች አጀንዳ ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን እና በተባበሩት መንግሥታት እና በሶማሊያ መካከል ካለው የዘላቂ ልማት ትብብር ማዕቀፍ ጋር የተጣመረ መሆኑን አስረድተዋል።

"ሶማሊያ ለኢንቨስትመንት ሰፊ አቅም አላት። ይህ ደግሞ ደግሞ ፖለቲካዊ መረጋጋት በማስፈን እና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ጥቅም ላይ መዋል አለበት። የንግድ ሁኔታውን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ያልተወሳሰበ የንግድ አመሰራረት፣ የምዝገባ ሂደት እና ፍቃድ አሰጣጥ ስርዓትን ይጠቃል። የመንግሥት አመራር እና ከግሉ ዘርፍ ጋር ያለው ትብብርም ዋና እና አስፈላጊ ነገር ነው። የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ከአጋሮች ጋር በመሆን ሶማሊያ በቅርቡ ወደ ብሩህ ወደሆነ መንገድ መጓዝ ትችላለች።"

የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ ለዓለም ህዝቦች ሰላም እና ብልፅግና ሊመጣ የሚችልበትን አቅጣጫ ይጠቁማል። ማንም ወደ ኃላ ሳይቀር ከዓለም ላይ ረሃብን ለማጥፋት፣ የምግብ እጥረትን ለማሻሻል፣ የፆታ እኩልነት እንዲኖር እና ሴቶች እና ልጃገረዶችን ለማብቃትም ግብ ሰንቋል።

በጉባኤው ላይ ተሳታፊ የነበሩት በሶማሊያ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ላሪ አንድሬ ጁኒየር በበኩላቸው በሶማሊያ ሙሉ የኢኮኖሚ መነቃቃት ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸው ዩናይትድ ስቴትስ በሶማሊያ እና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋማት መካከል ያለውን አጋርነት እንደምትደግፍ ጠቁመዋል።

ለ30 ዓመታት ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ሥርዓት ርቃ የቆየችው ሶማሊያ ከቅርብ አመታት ወዲህ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አና ዓለም ባንክ ከመሳሰሉ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት ተሻሽሏል።

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሀምዛ አብዲ ባሬም መንግስታቸው የኢኮኖሚ እና የደህንነት ህግጋት ማሻሻያዎች ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት አንፀባርቀዋል።

"በተሻለ ሁኔታ እንድናገለግላችሁ የሚያስፈልገውን ህጋዊና ተቋማዊ ሁኔታዎችን አዛጋጅተናል። ሶማሊያ እ.አ.አ በ2015 የውጭ መዋዕለ-ንዋይ ህግ አዘጋጅታ አፅድቃለች፣ የመዋዕለ-ንዋይ ፖሊሲዎችን የሚያወጣ የውጭ ኢንቨስትመንት ቦርድም መስርታለች። ይህ ህግ መዋዕለ-ንዋይ ይዘው የሚመጡ የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገር ውስጥ ካሉት እኩል እንዲታዩ የሚያደርግ ነው።"

ሶማሊያ በአፍሪካ ረዥሙ የባህር ዳርቻ ያላት ስፍራ፣ ለንግድ እና ለገበያ ያላት ተደራሽነት እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብቷ ቀዳሚ የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንደሚያደርጋት እና በኃይል፣ ቴክኖሎጂ፣ ባንክ እና ሌሎች የንግድ ዘርፎች በርካታ እድሎች እንዳሏት በስብሰባው ላይ ተጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG