ግዛቱን በመወከል የመጀመሪያው አፍሪካ-አሜሪካዊ የሆኑት ኮንግረስማን ዶናልድ ፔይን፤ ከመረጣቸው ህዝብ አልፈው በአለም ዙሪያ፣ በተለይ በአፍሪካ ለሰላምና ለልማት ሰርተዋል።
በንዋርክ ኒውጀርሲ በ1927 ዓ.ም የተወለዱት ኮንግረስማን ዶናልድ ፔይን፤ በ77 ዓመታቸው በዛሬውለት ያረፉት ባድረባቸው የካንሰር በሽታ ነው።
የፔይን ዜና እረፍት ብዙዎችን ያስደነገጠና ያልተጠበቀ ነበር። ባለፈው ወር ኮንግረስማኑ በህመም ላይ መሆናቸውን ገልጸው፤ ስራቸውን ግን እንደሚቀጥሉ ገልጸው ነበር።
ሆኖም በዛሬውለት ሞታቸው ሲሰማ፤ በቅርብ የሚያውቋቸው፣ በበጎ ስራቸው የሚያውቋቸውን አፍሪካዊያንና፤ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማንም ጭምር ያዛዘነ ዜና ነበር።
ከዋይትሃውስ ማምሻውን የወጣ መግለጫ፤ ፕሬዝደንቱ በዶናልድ ፔይን ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።