በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ የማይሰጥባቸው ት/ቤቶች እንዳሉ ተገለጸ


በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ የማይሰጥባቸው ት/ቤቶች እንዳሉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:38 0:00

· የተማሪዎቹ ወላጆች፥ “የልጆቻችን ዕጣ ፈንታ ያሳስበናል፤” እያሉ ነው

በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ችግር ባሉባቸው የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች፣ ትምህርት ካቋረጡ ከሦስት ዓመታት በላይ እንደኾናቸው፣ የቤተሰቦቻቸው አባላት ለአሜሪካ ድምፅ ተናገሩ።

በክልል ደረጃ፣ በቅርቡ የሚሰጠውን የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱትም፣ በከተማ እና በወረዳ ከተሞች ውስጥ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች እንደኾኑና እነርሱን እንደማያካትት፣ እነኚኹ የተማሪዎቹ ቤተሰቦች ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ሓላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ሂርኮ፣ በሁሉም ወረዳዎች፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተና ለመስጠት መዘጋጀቱንና ከ400ሺሕ በላይ ተማሪዎች፣ በዘንድሮው ዓመት በሚሰጠው የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል።

በኦሮሚያ ክልል፣ የሰሜን ምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪ እና የተማሪ ወላጅ እንደኾኑ ጠቅሰው፣ ለደኅንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ፣ “ቀደም ሲል በወረዳችን፣ ብዙ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ፥ ጎደጃባ፣ ሻካኬ፣ ቃሬ ቶከ፣ ኛኣ እና ቶሌንና አልዴራ የሚባሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን፣ በእነዚኽ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጧል።” በማለት በወረዳቸው ያለውን የመማር ማስተማር ሒደት አስመልክቶ አስተያየት ሰጥተዋል።

አክለውም፤ “ከሦስት ዓመት በፊት፣ ስምንተኛ ክፍል ደርሰው የነበሩ፣ አሁንም እዚያው ስምንተኛ ናቸው፡፡ ከአንድ እስከ ስምንት የነበሩ ሁሉም ተማሪዎች፣ ባሉበት ነው ያሉት። በተለይ፣ በቆላማ አካባቢው በሚገኙ 10 ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ ተማሪዎች፣ ምንም የመማር ዕድል አላገኙም። ምክንያቱም፣ በጸጥታ ችግር ትምህርት ቤቶቹ ሥራ በማቆማቸው ነው። በመኾኑም፣ በዘንድሮው የስምንተኛ ክፍል የመልቀቂያ ፈተና የሚቀመጡት፣ በወረዳው ከተማ ያሉ ተማሪዎች ብቻ ናቸው። ለወደፊቱ፣ የልጆቻችን ዕጣ ፈንታ አሳሳቢ ነው።” ብለዋል።

በኦሮሚያ ክልል በዋናነት የጸጥታ ችግር የተፈጠረው በክልሉ በሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂዎችና በመንግሥት የፀጥታ አስከባሪዎች መካከል ባለው ግጭችት ምክኒያት ሲኾን፤ ነዋሪዎቹ ሌሎች መደበኛ ያልኾኑ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሳሉ በሚሉበት አካባቢም በስጋት ምክኒያት ተማሪዎች ትምህርታቸውን መማር እንደተሳናቸው ያነጋገርናቸው ቤተሰቦች ገልፀዋል።

በሌላ በኩል የያያ ጉለሌ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በወረዳው፥ 400 ተማሪዎች፣ በስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ላይ ይቀመጣሉ።

የአሙሩ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ሓላፊ አቶ ዓለማየሁ ዋቅጅራ፣ ለአሜሪካ ድምፅ እንደተናገሩት፣ በወረዳቸው፥ ዘጠኝ የሚደርሱ የአንደኛ ትምህርት ቤቶች፣ በጸጥታው ምክንያት የመማር ማስተማር ሒደቱን መቋረጡን፤ ገለፀው “በ21 ትምህርት ቤቶች የሚገኙ 640 ወንድ ተማሪዎችንና 635 ሴት ተማሪዎችን፣ በአጠቃላይ 1ሺሕ275 ተማሪዎችን፣ በኦቦራ እና አገምሳ ክላስተር ላይ ለመፈተን ተዘጋጅተናል። በወረዳችን ዘጠኝ ትምህርት ቤቶች፣ በጸጥታ ችግር ሳቢያ ትምህርት እየተሰጠባቸው አልነበረም። በተቻለ መጠን፣ ተማሪዎች፥ ወደ ወረዳው ከተማ ተቃርበው እንዲማሩ ተደርጓል። አሁንም፣ ለፈተናው የሚቀመጡት እነርሱ ናቸው።” ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ፣ በሁሉም ወረዳዎች፣ የስምንተኛ ክፍል ፈተናን ለመስጠት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ፣ የተናገሩት የቢሮው ምክትል ሓላፊ ዶክተር ቡልቶሳ ህርኮ፣ “ፈተናውን፣ በሁሉም ወረዳዎች እንሰጣለን። ከጸጥታው ችግር ጋራ በተያያዘ፣ የመማር ማስተማር ሒደቱ ተቋርጦ በቆየባቸው ትምህርት ቤቶች ግን፣ ፈተና አይሰጡም። ቁጥራቸውን ለመግለጽ አሁን ዳታቸው የለኝም። በዚኽ ዓመት ለመፈተን ካቀድናቸው ተማሪዎች መካከል፣ 97ነጥብ2 የሚኾኑቱ ናቸው ለፈተናው የሚቀመጡት። ቀሪዎቹ፣ በጸጥታው ምክንያት እና በሌሎችም ችግሮች፣ ለፈተናው አይቀመጡም።” ብለዋል።

አሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው፣ የአንዳንድ ተማሪዎች ወላጆች፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ትምህርት መቋረጡን፤ ሲገልጹ የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ትምህርት ስለተቋረጠባቸው አካባቢዎች በአሀዝ አስደግፎ ከመግለጽ ተቆጥቧል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ውስጥ ከትምህርት በተጨማሪ ሌሎች የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ እንደተሳናቸው ነዋሪዎች ከዚህ ቀደም ሲገልጹ ቆይተዋል።

/ሙሉ ዘገባውን ተያያዘው የድምፅ ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG